ቀጥታ፡

በከተማችን የሰፈነው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን የድርሻችንን እንወጣለን - የኃይማኖት አባቶች

ደሴ ፤ ሕዳር 29/2018(ኢዜአ)፦በደሴ ከተማ የሰፈነው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ የከተማዋ የኃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

በደሴ ከተማ ታላቅ የሰላም ጥሪን ያነገበ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ ተካሂዷል።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደር እና የደቡብ ወሎ ዞን የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባዘጋጁት የድጋፍ ሰልፍ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መላከ ሰላም ፈንታ አበራ እንዳሉት፣ ሁሉም ለዘላቂ ሰላምና አንድነት በጋራ መስራት አለበት።

ለዘላቂ ሰላማችንና አንድነታችን ቅድሚያ በመስጠት እንደ ኃይማኖት አባት የሚጠበቅብንን ድርሻ በላቀ ትጋት እንወጣለን ሲሉም ገልጸዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ሀሰን ሀሚዲን በበኩላቸው፣ የሁሉም ቤተ እምነቶች ሰላምን ማስፈን ተቀዳሚ ተግባራቸው በማድረግ የሰላምና የመከባበር ባህልን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ያለ ልዩነት ዘላቂ ሰላምን ማስፈን፣ ልማታችንን በጋራ ማስቀጠልና አንድነታችንን ማጠናከር  ይገባናል ብለዋል።


 

እኛም ሕብረተሰቡን በማስተባበር፣ በመምከርና በማስተማር  ሰላም እንዲጸና ከፊት ሆነን የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉም ሸህ ሀሰን አክለዋል።

ሰላምና አንድነትን ለማጽናት እጅ ለእጅ ተያይዘን ግንባር ቀደም ሆነን በቅንጅት እንሰራለን ያሉት ደግሞ የደሴ መካነኢየሱስ ቤተክርስቲያን ቄስ መስፍን ጌታሁን ናቸው።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ፣ የደሴ ከተማና የደቡብ ወሎ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዛሬ ያዘጋጁት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ሰላማችንን ከማጽናት ባለፈ የከተማችን ልማት እንዲፋጠን ለአመራሩ አቅሞ፣ ሞራልና ጉልበት የሚጨምር ነው ብለዋል።

ሕብረተሰቡ አንድነቱን ጠብቆ የአባቶችን ምክርና ሀሳብ በማድመጥ የአብሮነት፣ የሰላምና የመቻቻል ባህሎችን ማስቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ነዋሪዎች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም