ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ የክልሉ ሕዝብ ቁርጠኛ ነው -እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ የክልላችን ሕዝብ ትጋቱን ይቀጥላል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለጹ።

ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት በሚል መሪ ሃሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እየተከበረ ይገኛል።

ቀኑ እየተከበረ የሚገኘው “ዴሞክራሲያዊ መግባባት፤ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ ነው።

በዚሁ ወቅት ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፤ በዓሉ ብሔራዊ መግባባትን በማጠናከር የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደትን ለማሳለጥ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።

በተጨማሪም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በአንድ መድረክ ተገኝተው እንዲደምቁና እንዲመክሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን ባህላዊ ትውፊታቸውንና ልምዶቻቸውን የሚለዋወጡበት ዕድል መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።


 

ለወንድማማችነትና እህትማማችነት ዕሴቶች ማበብ እንዲሁም ለኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ፌዴራሊዝም መዳበር ብሎም ለጋራ ትርክት ግንባታ በዓሉ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ቀጥሏል ብለዋል።

ቀኑ በሐሳብ ልዕልና በመመራት ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት የመመካከርና የመወያየት ባህልን በማላቅ የዳበረ የዴሞክራሲና የአካታችነት ባህልና እሴቶችን ለማስረጽ እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ ይወሰዳል ሲሉም ገልጸዋል።

የምግብ ሉዓላዊነትን በጋራ ጥረት እውን በማድረግ ሀገራችን ክብሯ የተሟላ እንዲሆን የብልጽግና ጉዞዋም እንዲሳካ የተጀመሩ ጥረቶች እንደ ክልል ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የሀገራችንን ብሔራዎ ጥቅሞች ለማስከበርና አዳጊ የሕዝቦች ፍላጎትን ለማሟላት መሠረታዊ ሆኑ እንደ ባሕር በር ያሉ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በሚደረገው እንቅስቃሴ የክልላችን ሕዝቦች የበኩላቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ ናቸው ብለዋል በንግግራቸው።

ቀኑ በክልላችን መከበሩ ለክልላችን ዘርፈ ብዙ ፋይዳና ትርጉም እንዳለውም እንገነዘባለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም