በቅርስ ጥበቃና አያያዝ ስኬታማ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቅርስ ጥበቃና አያያዝ ስኬታማ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 29/2018(ኢዜአ)፦ በመደመር መንግሥት እይታ በቅርስ ጥበቃና አያያዝ ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ህይወት ሀይሉ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ህይወት ሀይሉ፣ የኦሮሚያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን ታምሩ፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት የዓለም ቱሪዝም ቀንን አስመልክቶ በምስራቅ ባሌ ዞን የሚገኘውን የድሬ ሼኽ ሁሴን ታሪካዊ ቦታ ጎብኝተዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ህይወት ሀይሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን በማደስና በማልማት የቱሪዝም ማዕከል እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው።
በዚህም ለረጅም ጊዜ ትኩረት ያልተሰጣቸውን ታሪካዊ ቦታዎች በማልማትና ነባሮቹን በተሻለ መልኩ በመጠገን ሃብታቸው በአግባቡ እንዲገለጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር መዳረሻዎቹን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ የመንገድ፣ የሆቴል እና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በመደመር መንግሥት እይታ በቅርስ ጥበቃና አያያዝ ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቅርሶች ቁጥር እንዲጨምር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህ ረገድ በምስራቅ ባሌ ዞን የሚገኘውን የድሬ ሼኽ ሁሴን ታሪካዊ ቦታ በዩኔስኮ የጊዜያዊ ዝርዝር ውስጥ በማስገባት የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን ታምሩ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚገኙትን ቅርሶች ለመጠበቅ፣ ለማልማትና ለማስተዋወቅ ሰፊ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ትኩረት ከተሰጣቸው ቅርሶች መካከል በምስራቅ ባሌ ዞን የሚገኘው የድሬ ሼኽ ሁሴን ታሪካዊ ቦታ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ወደ ድሬ ሼኽ ሁሴን ታሪካዊ መዳረሻ የሚወስድ የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ይህም የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ፣ ቅርሱን ይበልጥ ለማልማት፣ ለማስተዋወቅና በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።