በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 29/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ የሁለተኛ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይደረጋሉ።
ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ አዳማ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ይጫወታሉ።
አዳማ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 10 ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፍ አምስት ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ላይ ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር 19 ጎሎችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ13 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ ማሸነፍ የቻለው ጨዋታ አንድ ብቻ ነው። ስምንት ጊዜ ሲሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይቷል። አምስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 22 ግቦች ተቆጥረውበታል። በአራት ነጥብ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃን ይዟል።
በሌላኛው መርሃ ግብር መቻል ከባህር ዳር ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በሊጉ ካከናወናቸው 10 ጨዋታዎች መካከል ስድስቱን ያሸነፈው መቻል ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 17 ግቦችን በ10ሩ ጨዋታዎች ላይ ሲያስቆጥር ሰባት ግቦችን አስተናግዷል።
መቻል በ20 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ በውድድር ዓመቱ 10 ጨዋታዎችን አድርጎ አንድ ጊዜ አሸንፎ በስምንቱ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል። አምስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 15 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ባህር ዳር ከተማ በአራት ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
የዕለቱ የመጨረሻ መርሃ ግብር ልደታ ክፍለ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ያገናኛል።
ልደታ ክፍለ ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው 10 ጨዋታዎች ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በሰባቱ ሲሸነፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል። በ10ሩ ጨዋታዎች ላይ ሰባት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 19 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በአምስት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በሊጉ ካደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ አራት ጊዜ ተሸንፏል። ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ መውጣት ችሏል። ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ጎሎችን አስተናግዷል።
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሲዳማ ቡና በዘጠኝ ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።