የቀኑ መከበር የአብሮነት እሴትን በማዳበር ለሀገራዊ እድገት ተደማሪ አቅም ይሆናል - ኢዜአ አማርኛ
የቀኑ መከበር የአብሮነት እሴትን በማዳበር ለሀገራዊ እድገት ተደማሪ አቅም ይሆናል
ሆሳዕና ፤ሕዳር 28/2018 (ኢዜአ)፡- የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር የአብሮነት እሴትን በማዳበር ለሀገራዊ እድገት ተደማሪ አቅም እንደሚሆን በብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በማስመልከት የተዘጋጀ ሲምፖዝየም ተሳታፊዎች ገለጹ።
20ኛውን የብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በማስመልከት የተዘጋጀ ሲምፖዝየም በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል፡፡
በሲምፖዝየሙ ከተሳተፉ መካከል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጡት አቶ አብድልመሀሙድ ኢብራሂም ለኢዜአ እንዳሉት፤ የቀኑ መከበር የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር ለሀገራዊ እድገት ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል።
በአብሮነት መጓዝ ለስኬት እንደሚያበቃ ከታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ መማር እንደሚቻል በማሳያነት አንስተዋል፡፡
ይህን ተሞክሮ በማስቀጠል የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን የሚያደርጉ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ከግብ ለማድረስ በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።
ለዚህም ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ አክለዋል።
ከሀረሪ ክልል የተሳተፉት አቶ ሰይድ አብዱራህማን በበኩላቸው፡የኢትዮጵያን የለውጥ ግስጋሴ ከግብ ለማድረስ የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በልማቱ የዜጎችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ህብረ ብሄራዊነት ላይ ይበልጥ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ተግባሩን ለማሳካትም ለሰላም አጥብቆ በመስራት ሀገራዊ እድገትን ማዝለቅ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል በመምጣት በሲምፖዝየሙ የተሳተፉት ሀደ ስንቄ ሸምሲያ ጉመህ በበኩላቸው፤ የመደመር መንግስት የአብሮነት እሴትን በማጉላት እንደ ሀገር ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳየቱን ጠቁመዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ ያሏትን ፀጋዎች በማልማት ለትውልዱ ብልፅግናዋን ማውረስ እንደምትችል በተጨባጭ ማሳየቷን አክለዋል።
ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ማፅናት ሁለንተናዊ ለውጥን በጋራ ለማስቀጠል መሰረት እንደሚጥል ገልጸዋል፡፡
20ኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ነገ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳእና ከተማ ይከበራል።