ቀጥታ፡

የፌዴራዝሊም ስርዓቱ የብዝሃ ማንነትን መብት ባከበረ መልኩ እየተተገበረ  ነው- አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር 

ሆሳዕና፤ ሕዳር 28/2018(ኢዜአ)፡-  ኢትዮጵያ የመልከ ብዙ ባሕላዊና  ታሪካዊ  እሴቶች መገለጫ በመሆኗ የተከተለችው የፌዴራሊዝም ስርዓት የብዝሃ ማንነትን መብት ባከበረ መልኩ እየተተገበረ   መሆኑን   የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።  

ነገ የሚከበረው  የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን  ምክንያት በማድረግ   የተዘጋጀ  ሲምፖዚየም  ዛሬ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል።


 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ  አገኘሁ ተሻገር በወቅቱ  እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን ወደ ታለመላት የእድገትና ብልፅግና ተርታ ለማድረስ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል፡፡

በፌዴራሊዝምና በህገ መንግስቱ ዙሪያ  የዜጎችን የጋራ ግንዛቤ በማሳደግ ሕብረ ብሔራዊ  አንድነትን አጠናክሮ   ዘላቂ ሰላም፣ ፈጣን ልማትና እድገትን ለማረጋገጥ  ሁሉም መትጋት እንዳለበት አንስተዋል።

ባለፉት ዓመታት  በተለይም ከለውጡ ወዲህ ሲከበር የቆየው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የሕዝቦችን የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴት እንዲጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  እሴቶቻቸውን ፣ ልምዶቻቸውን ፣ ባሕሎቻቸው  እንዲጎለብትም እንዲሁ። 

20ኛው  የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ከሕዳር 1 ጀምሮ በየክልሎቹ በፓናል ውይይት ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና  በሌሎች  ኹነቶች  ሲከበር ቆይቶ አሁን በማጠቃለያው ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል። 


 

በዓሉ  የሀገሪቱ ዜጎች የአብሮነት ውጤት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ በተመረቀበትና ሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በተጀመረበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ  የመልከ ብዙ የባሕልና ታሪካዊ  እሴቶች መገለጫ በመሆኗ  የተከተለችው የፌዴራሊዝም ስርዓት  የብዝሃ ማንነትን መብት ባከበረ መልኩ እየተተገበረ   መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ለትውልዱ እንዲተላለፍ  ሲከናወን የቆየው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

የፌደራሊዝምን ስርዓቱን በመጠበቅ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ  ክልል ርዕስ መስተዳደር  እንዳሻው ጣሰው  (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በአደባባይ መከበሩ ብዝሀነት  አስጠብቆ  በማዝለቅ ሀገራዊ ፋይዳውን ለማጉላት ያግዛል።


 

የመደመር እሳቤዎችን በመተግበር የመጡ ለውጦችን  አጠናክሮ በማስቀጠል  የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን  ይበልጥ  ማጠናከር  እንደሚገባ አመልክተዋል። 

የጋራ ትርክትን  አጠናክሮ   የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደትን በማፋጠን   ድህነትን ማሸነፍ   እንደሚገባ  አንስተው፤ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን  መጠበቅና ማስከበር አለብን ብለዋል። 

ከሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች መካከል  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት ፤ ተቀናጅቶ መስራት ሀገራዊ ለውጡን ከግብ ማድረስ እንደሚቻል የሕዳሴው ግድብ   ማሳያ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡


 

ችግሮችን  በውይይት በመፍታት እንደ ሀገር   የተጀመረውን ለውጥ አጠናክሮ ለጋራ ብልፅግና መትጋት የሁሉም ቅንጅታዊ ተግባር  መሆን እንዳለበት አንስተዋል፡፡

መተኪያ የሌላትን ሀገር  ሰላምና ልማት የማጠናከር ስራ  የኛ  የዜጎች  ሀላፊነት ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው  ተሳታፊ አቶ አህመድ መሐመድ  ናቸው።


 

ለዚህም  ከነጣጣይ ትርክት ይልቅ አብሮነትንና አሰባሳቢ ትርክትን  በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በማተኮር  የብልፅግናውን  ጉዞ ለማሳካት መረባረብ ይገባናል ሲሉ አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም