ቀጥታ፡

አፍሪካውያን የበለጸገች አህጉር ለመፍጠር በጠንካራ አንድነትና በጋራ ዓላማ ሊቆሙ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 28/2018 (ኢዜአ)፦አፍሪካውያን የበለጸገች አህጉር የመፍጠር የጋራ ራዕይን ለማሳካት በጠንካራ አንድነትና በጋራ ዓላማ ሊቆሙ እንደሚገባ ተገለጸ።

የቀድሞ የአፍሪካ መሪዎችና የፓን አፍሪካ አቀንቃኞች ልጆችና የልጅ ልጆች፣ የመንግሥት አመራሮች፣ ምሁራን እና ተማሪዎች  ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ የነጻነት ትግል ውስጥ ያላትን የቀደመ ታሪክ እና ቀጣይነት ያለው ተምሳሌታዊ ሚና በተመለከተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክክር አድርገዋል።


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፥ አፍሪካ በውስጣዊ ችግሮችና ከውጭ በሚመጡ ጫናዎች እየተፈተነች እንደምትገኝ ጠቅሰው፥ ይህን ለመሻገር ትግል ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

አፍሪካ ሰላምንና ብልጽግናዋን በማረጋገጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ መሪ ሚና እንዲኖራት የዚህ ዘመን ትውልድ የቀደምት አፍሪካውያን አባቶችን የአንድነትና የጥበብ ፈለግ መከተል እንዳለበት አፅንዖት ሰጥተዋል። 


 

በህብረት በመቆም አሸናፊ መሆንና እና መበልጸግ እንደምንችል  ከቅድመ አያቶቻችን ተምረናል ነው ያሉት።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካ ንቅናቄ ውስጥ ጉልህ ሚና እንዳላት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያውያን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በራሳቸው አቅም ማሳካት መቻላቸው በህብረት መቆም ያለውን ፋይዳ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

ሀገራት በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ብቻ ሳይገደቡ አብረው መስራት ከቻሉ አስደናቂ ልማትና ዕድገት ማስመዝገብ ይችላሉ ብለዋል። 

አፍሪካ ትልልቅ ግቦችን የማሳካት አቅም አላት ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ለዚህ ደግሞ  ጠንካራ ህብረትና የጋራ ዓላማ ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጋና የመጀመሪያው ፕሬዝዳንትና የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ የነበሩት ክዋሜ ንክሩማህ ሴት ልጅ ሳሚያ ንክሩማህ አፍሪካ ትልቅ ህዝብ እንዳላትና ይህም ህልሞቿን እንድታሳካ የሚያስችል ጸጋ ነው ብለዋል።  


 

የአህጉሪቱ ወጣቶች ህብረት ለውጥ ለማምጣት ታላቅ ኃይል መሆኑን መረዳት እንዳለባቸው ጠቁመው ኢትዮጵያውያን ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በጋራ መገንባት መቻላቸው አፍሪካውያን ሲተባበሩ ትልልቅ ግቦችን እንደሚያሳኩ የተግባር ምሳሌ ነው ብለዋል።

የ1950ዎቹና 60ዎቹ ትውልድ አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ነጻ ማውጣቱን ጠቅሰው፥ የዚህ ዘመን ትውልድ ደግሞ ድህነትን፣ ስራ አጥነትንና የኢኮኖሚ ጥገኝነትን ለማስወገድ የቀደምት አፍሪካውያንን ታሪክ በሚገባ በማወቅ የመነሳሳት ምንጭ ሊያደርጉት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የቀድሞው የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ የወንድም ልጅ እና የአፍሪካ ሌጋሲ ፋውንዴሽን ዋና ፀሐፊ ሙሳ ኢብራሂም ጋዳፊ አዲሱ ትውልድ በተለይም የአፍሪካ ምሁራን እና ተማሪዎች የቀደሙት መሪዎች ያጸኑትን  የትብብር፣ የአይበገሬነት እና የጋራ ራዕይ የማስቀጠል ሃላፊነት እንዳለባቸው አስረድተዋል። 


 

በአፍሪካ ሀገራት መካከል የሚኖር ጠንካራ ህብረት፣ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር እና ዘመኑን የዋጀ የጋራ የልማት አጀንዳ ለማራመድ አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም  ለስኬቱ እንዲተጋ ጥሪ አቅርበዋል። 

አፍሪካን ማዕከል ያደረገ የትምህርት ስርዓት ለመቅረጽ ትብብርን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ የአፍሪካ የልማት ምሰሶ ሆና እንድትቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።


 

የፓናል ውይይቱ  ተሳታፊዎች በአፍሪካ ወጣቶች መካከል መተማመን፣ ህብረትና የጋራ ሃላፊነት እንዲፈጠር ማስቻል አስፈላጊ በመሆኑ መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ትውልዱን በአርዓያነት መቅረፅ እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም