በመደመር እሳቤዎች የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ይበልጥ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር እሳቤዎች የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ይበልጥ ይጠናከራል
ሆሳዕና፤ ሕዳር 28/2018 (ኢዜአ)፦ የመደመር እሳቤዎችን በመተግበር የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሕብረ ብሄራዊ አንድነት ይበልጥ እንደሚጠናከር ተገለጸ።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ " ዴሞክራሲያዊ መግባባት ፣ ለሕብረ ብሄራዊ አንድነት " በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ሲምፖዚየም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።
በሲምፖዚየሙ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እንዳመለከቱት፤የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በአደባባይ መከበሩ ብዝሀነትን አስጠብቆ በማዝለቅ ሀገራዊ ፋይዳውን ለማጉላት ያግዛል።
የመደመር እሳቤዎችን በመተግበር የመጡ ለውጦችን አጠናክሮ በማስቀጠል የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።
የጋራ ትርክትን አጠናክሮ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደትን በማፋጠን ድህነትን ማሸነፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያሉ ፀጋዎችን አልምቶ የሕዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በተቀናጀ መንገድ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አንስተዋል።
ከሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት ፤ ተቀናጅቶ በመስራት ሀገራዊ ለውጡን ከግብ ማድረስ እንደሚቻል የሕዳሴው ግድብ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ችግሮችን በውይይት በመፍታት እንደ ሀገር የተጀመረውን ለውጥ አጠናክሮ ለጋራ ብልፅግና መትጋት የሁሉም ቅንጅታዊ ተግባር መሆን እንዳለበት አንስተዋል፡፡
መተኪያ የሌላትን ሀገር ሰላምና ልማት የማጠናከር ስራ የኛ የዜጎች ሀላፊነት ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው ተሳታፊ አቶ አህመድ መሐመድ ናቸው።
ለዚህም ከነጣጣይ ትርክት ይልቅ አብሮነትንና አሰባሰቢ ትርክትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የብልፅግናውን ጉዞ ለማሳካት መረባረብ ይገባናል ሲሉ አመላክተዋል፡፡