ቀጥታ፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ ሆነው ያሳኩት የኀብረትና አንድነት ውጤት ነው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 28/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ ሆነው ያሳኩት የኀብረትና አንድነት ውጤት ነው ሲሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለጹ።

አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያዊያን የጋራ ርብርብና ጥረት እውን ሆኗል።

ሕዝቡ በቦንድ ግዥ፣ በገንዘብ ስጦታ፣ በጉልበት፣ በጥሬ ዕቃ ድጋፍ ፣ ስፖርታዊ ውድድሮችን ጨምሮ በተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።


 

በተለያዩ ክልሎች ሲዘዋወር በቆየው የህዳሴ ግድብ ዋንጫም ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ተገኝቷል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ግድቡ በራስ አቅም እውን እንዲሆን ዓይነተኛ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል።

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከቦንድ ሽያጭ፣ በገንዘብ ስጦታ፣ 8100Aን በሚል በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መንገድን ጨምሮ ከተለያዩ ገቢ መሰብሰቢያ አማራጮች በጥቅሉ ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ ከሕዝቡ በድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

በክልሎች ሲዘዋወሩ በቆየው ዋንጫ አማካኝነት ስድስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አመልክተው፤ ይህም የህብረትና አንድነት ውጤት ነው ብለዋል።

በዓድዋ ጦርነት ብሄር ብሄረሰቦች በህብረት ታግለው አኩሪ ድል አስመዝግበዋል ያሉት አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ ያሳኩት ዳግማዊ የዓድዋ ድል ነው ሲሉም ተናግረዋል።


 

ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫን ለገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከፌደሬሽን ምክር ቤት መረከቡን አስታውሰው፤ የግድቡ ግንባታ በመጠናቀቁ ዋንጫው በ20ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ክብረ በዓል ላይ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚመለስም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከተባበሩ የማያሳኩት የልማት አጀንዳ እንደሌለ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማሳያ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ሌሎች የልማት ግቦችንም ለማሳካት የሚደረገው ርብርብ ሊጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

አይቻልም የሚለው አስተሳሰብ ቦታ የሌለው መሆኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማረጋገጫ የሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም