የጋራ ውሳኔ ሰጪነትን በማረጋገጥ የሕዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ ውሳኔ ሰጪነትን በማረጋገጥ የሕዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ተጠናክሮ ይቀጥላል
ሆሳዕና፤ ሕዳር 28/2018(ኢዜአ)፡- የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀገር በሆነችው ኢትዮጵያ የጋራ ውሳኔ ሰጪነትን በማረጋገጥ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
ነገ የሚከበረው 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ በሆሳዕና ከተማ " ዴሞክራሲያዊ መግባባት ፣ ለሕብረ ብሄራዊ አንድነት " በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በሲምፖዚየሙ መከፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያን ወደ ታለመላት የእድገትና ብልፅግና ተርታ ለማድረስ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል፡፡
በፌዴራሊዝምና በሕገ መንግስቱ ዙሪያ የዜጎችን የጋራ ግንዛቤ በማሳደግ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን አጠናክሮ ዘላቂ ሰላም፣ ፈጣን ልማትና እድገትን ለማረጋገጥ ሁሉም መትጋት እንዳለበት አንስተዋል።
በባለፉት ዓመታት በተለይም ከለውጡ ወዲህ ሲከበር የቆየው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴት እንዲጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እሴቶቻቸውን ፣ ልምዶቻቸውን እና ባሕሎቻቸው እንዲጎለብት ማድረጉንም አመልክተዋል።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ከሕዳር 1 ቀን 2018 ጀምሮ በየክልሎቹ በፓናል ውይይት ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና በሌሎች ኹነቶች ሲከበር ቆይቶ አሁን በማጠቃለያው ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ዜጎች የጋራ ውሳኔ ሰጪነታቸውን በማረጋገጥ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
በዓሉ የመላው የሀገሪቱ ዜጎች የአብሮነት ውጤት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ በተመረቀበትና ሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ዓመቱ 7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚካሄድበት ስለመሆኑ ያነሱት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘው ተሻገር ፤ ምርጫው በሕዝቦች ሰፊ ተሳትፎ ሰላማዊና ፍትሀዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ምርጫው ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት ፣ ለፍትሀዊ ተጠቃሚነትና ለዲሞክራሲ ባሕል ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅሰው፤ ለስኬታማነቱም ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡
20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ብዝሀ ማንነትን ባከበረ በደመቀ መልኩ እንደሚከበርም ተናግረዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋጤ ስርሞሎ በበኩላቸው ፤ በዓሉ የኢትዮጵያውያን የእርስ በእርስ ትስስር ይበልጥ የሚጠናከርበት መሆኑን ገልጸዋል።
የበዓሉ መከበር የሕገ መንግስትና የፌዴራሊዝም አስተምህሮ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ የሀገረ መንግሥት ግንባታው እንዲጠናክር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አንስተዋል።
በሲምፖዚየሙ ላይ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ፣ የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች፣ የባሕል አምባሳደሮችና ተጋባዥ እንግዶች እየተሳተፉ ነው፡፡