ቀጥታ፡

አመራሩ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል በመቀየር ለላቀ ስኬት መትጋት አለበት

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 28/2018 (ኢዜአ)፦አመራሩ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል በመቀየር ለላቀ ስኬት መትጋት አለበት ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

“በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ ለተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የቆየው 3ኛ ዙር የወረዳ አመራሮች ስልጠና ተጠናቋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማጠቃለያው ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሀገራችንና በመዲናዋ እየተመዘገቡ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ድሎች አመራሩ እና ህዝቡ በቅንጅት ሰርተው ያሳኳቸው ናቸው ብለዋል።  

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የስንዴ ልማትና የኮሪደር ልማትን ጨምሮ፥ በሀገራችንና በአዲስ አበባ የተመዘገቡ አስደናቂ ለውጦች ለበለጠ ስራ የሚያነሳሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የአመራር ስልጠናው በአዲስ ዕይታ ለተጨማሪ ስኬት መትጋት የሚያስችል የእውቀትና የአመለካከት አቅም የተፈጠረበት እንደሆነም ገልጸዋል።

አመራሩ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል በመቀየር ለላቀ ውጤት መትጋት እንዳለበት ያነሱት ከንቲባ አዳነች፥ በሁሉም ዘርፍ አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።


 

ለዚህም በማያቋርጥ የአመለካከት፣ የስነምግባርና የባህሪ ግንባታ ራስን ማብቃት አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

ስልጠናው በግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን፤ በኢንዱስትሪ፤ በከተማ ልማትና በቱሪዝም ዘርፎች ላይ ያተኮረ መሆኑን አንስተው፥ ስልጠናው በተሰናሰለ የዘርፎች እመርታ መዋቅራዊ ሽግግርንና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማሳካት መግባባት የተፈጠረበት ነው ብለዋል።

ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተቀመጡ ሀገራዊ ግቦችን ለማሣካት አመራሩ በመፍጠርና መፍጠን መርህ መሥራት እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም