የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ብዝኃነት የደመቀበት ዕለት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ብዝኃነት የደመቀበት ዕለት ነው
አሶሳ፤ ሕዳር 28/2018 (ኢዜአ)፦ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ብዝሃነት የደመቀበት እለት መሆኑን በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር አዳሙ ጅባት ተናገሩ።
ህገ መንግስቱ የፀደቀበትን ቀን መነሻ በማድረግ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ዘንድሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለ20ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች በነገው ዕለት ይከበራል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር አዳሙ ጅባት እንደተናገሩት፤ ቀኑ ህገ መንግስቱ ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የሰጠውን እኩል መብት በአደባባይ የሚንፀባረቅበት ነው።
ቀኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በአንድነት የሚያከብሩት በመሆኑ ብዝሃነት የደመቀበት እና የእርስ በርስ ግንኙነት የተጠናከረበት ነው ብለዋል፡፡
በዓሉ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሀገራዊ አጀንዳዎች የሚተላለፉበት እና ሁሉንም ዜጋ የሚያስተሳስሩ ተግባራት የሚንሸራሸሩበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የፌዴራሊዝም ስርዓት የብዝሃነት እና የአንድነትን ሚዛን ማስጠበቅ ነው ያሉት መምህር አዳሙ፥ በሀገር ደረጃ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችም ይህንን እሳቤ የሚያሳዩ እንደሆነ ገልጸዋል።
"ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል የሚከበረው 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን የዴሞክራሲ ባህልን የሚያጎለብት እና ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሁሉም ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን የሚያመላክት እንደሆነ ጠቁመዋል።
ይህም ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር እና የጋራ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለመፍጠር የሚያግዝ ነው ብለዋል።