ቀጥታ፡

ቀኑ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል- አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

ሆሳዕና ፤ ሕዳር 28/2018(ኢዜአ)፡-  የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የህዝቦችን ትስስር በማጎልበት ሕብረ ብሔራዊ አንድነት  እንዲጠናከር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን  የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ  አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።  

በነገው ዕለት  የሚከበረውን 20ኛው  የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ   " ዴሞክራሲያዊ መግባባት ፣ ለሕብረ ብሄራዊ አንድነት " በሚል መሪ ሀሳብ  የተዘጋጀ  ሲምፖዚየም በመካሄድ ላይ ነው።

በሲምፖዚየሙ መክፈቻ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ  አገኘሁ ተሻገር  እንደገለጹት፤ በዓሉ መከበር ከጀመረ ወዲህ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  እሴቶቻቸውን፣ልምዳቸውን እና  ባሕላቸውን በማስተዋወቅና የክልሎችን ገፅታ በመገንባት  ትርጉም ያለው ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።   


 

በተለይም ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል እህትማማችነትና ወንድማማችነትን በማጎልበት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር  ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን  አስታውቀዋል።   

የዘንድሮው  የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል  ታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ በተመረቀበትና ሌሎች የተለያዩ አዳዲስ  ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ወቅት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ አፈ ጉባዔው ገልጸዋል።   

በዓሉ ኢትዮጵያ በማንሰራራት በውጤታማነት እየገሰገሰች ባለችበት ወቅት የሚከበር መሆኑም እንዲሁ። 


 

በሲምፖዚየሙ ላይ  በፌዴራሊዝም ፅንሰ ሀሳብ ዙሪያ የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበትና ቀጣይ አቅጣጫዎችም እንደሚመላከት ይጠበቃል። 

በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ  አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ፤ የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች ፡ የባሕል አምባሳደሮችና ተጋባዥ እንግዶች እየተሳተፉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም