ቀጥታ፡

በሊጉ ፋሲል ከነማ ከመቀሌ 70 እንደርታ ሃዋሳ ከተማ ከመቻል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 28/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ በሚደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል። 

ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ፋሲል ከነማ ከመቀሌ 70 እንደርታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ፋሲል ከነማ በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አራት ጊዜ አቻ ወጥቷል። ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ16 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው መቀሌ 70 እንደርታ ከስምንቱ የሊግ ጨዋታዎች በአራቱ ሲሸነፍ በቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። ስምንት ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 13 አስተናግዷል።

መቀሌ 70 አንደርታ በአራት ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ፋሲል ከነማ መልካም ጅማሮውን ለማስቀጠል በአንጻሩ መቀሌ 70 አንደርታ በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ። 

በሌላኛው መርሃ ግብር ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ሃዋሳ ከተማ ከመቻል በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ሃዋሳ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች መካከል አራቱን ሲያሸንፍ በሶስቱ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር ስድስት ግቦችን አስተናግዷል።  

ቡድኑ በ13 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  

ተጋጣሚው መቻል በበኩሉ በውድድር ዓመቱ ባከናወናቸው ስምንት ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ብቻ ሽንፈት አጋጥሞታል። በአራት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። 12 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ስምንት ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

መቻል ከተጋጣሚው ጋር ተመሳሳይ 13 ነጥብ በመያዝ በግብ ክፍያ በልጦ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በሊጉ መልካም ጅማሮ ያሳዩት ሁለቱ ቡድኖች በጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።   

በሌሎች መርሃ ግብሮች ሀዲያ ሆሳዕና ከነጌሌ አርሲ ከቀኑ 9 ሰዓት፣ አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ምሽት 12 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም