ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 28/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይካሄዳሉ። 

ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ሃዋሳ ከተማ ከይርጋጨፌ ቡና ይጫወታሉ። 

ሃዋሳ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው 10 ጨዋታዎች መካከል ሰባቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። 21 ግቦችን ሲያስቆጥር ዘጠኝ ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ22 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

አዲስ አዳጊው ይርጋጨፌ ቡና በሊጉ ባከናወናቸው 10 ጨዋታዎች ያሸነፈው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው። አራት ጊዜ ሲሸነፍ በተመሳሳይ አራት ጊዜ አቻ ወጥቷል። አራት ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 12 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

ይርጋጨፌ ቡና በ10 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።  ጨዋታው ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው። 

በሌላኛው መርሃ ግብር ሸገር ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በሊጉ ባከናወናቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ስድስቱን ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። በጨዋታዎቹ ላይ 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሸገር ከተማ በ18 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 10 ጨዋታዎች በሁለቱ ተሸንፎ በስድስቱ ሽንፈት አስተናግዶ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል። ቡድኑ ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ጎሎች አስተናግዷል። 

አርባምንጭ ከተማ በስምንት ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት እስከ ሕዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሊጉን በ30 ነጥብ እየመራ ነው። ባህር ዳር ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ 13ኛ እና 14ኛ ደረጃን ይዘው ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞን በ16 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራች ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ረድኤት አስረሳኸኝ በስምንት ጎሎች ትከተላታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም