ቀጥታ፡

በአራተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ ውድድር ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ሽኝት ተደረገ

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ በአንጎላ ሉዋንዳ በሚካሄደው በአራተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ ውድድር ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ማምሻውን ሽኝት ተደርጓል። 

ውድድሩ ከታህሳስ 1 እስከ ታህሳስ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል። 

ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ በሁለቱም ጾታዎች በሰባት የስፖርት አይነቶች 70 ስፖርተኞችን ታሳትፋለች። 

አትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ካራቴ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ውሃ ዋና እና ክብደት ማንሳት ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው። 

የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ማምሻውን ለልዑካን ቡድኑ የሽኝት መርሃ ግብር አካሂዷል። 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የስፖርት ልማትን ለማሳደግ ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት ታዳጊ ወጣቶች ላይ በመስራት በአህጉር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ  መድረክ ተወዳዳሪና ውጤታማ ስፖርተኞች ማፍራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

አክለውም ተተኪ ስፖርተኞች በማፍራት ሀገርን በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ መወከል ትልቅ ስኬት ነው ያሉት ሚኒስትሯ ተሳታፊ ስፖርተኞች ከአንጎላ ሉዋንዳ በድል እንዲመለሱ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን መሪ  አቶ ገዛኸኝ ወልዴ የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞች በቅርቡ በተካሄደው ሁለተኛው የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ ባስመዘገቡት ውጤት የተመረጡ ናቸው ብለዋል። 

በአንጎላ በሚካሄደው ውድድር ስፖርታዊ ጨዋነትን በመላበስ ለውጤት ለመብቃት እንደሚሰሩ እና በቀጣይም ዳካር በሚደረገው ውድድር ለመሳተፍ በአንጎላ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ ገልጸዋል።

የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ቡድኑን በማበረታታት መልካም ምኞታቸውን  በመግለጽ ለልዑካን ቡድኑ ሰንደቅ አላማ ማስረከባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል። 

በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ  መኪዩ መሐመድ ጨምሮ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሜቴ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት፣ የብሔራዊ ፌዴራሽን ፕሬዚዳንቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በአራተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና 54 ሀገራት በ33 የስፖርት አይነቶች ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም