ከተማዋን የማልማት ተግባር ባለሀብቱን እና ነዋሪውን ባሳተፈ መልኩ በቅንጅት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከተማዋን የማልማት ተግባር ባለሀብቱን እና ነዋሪውን ባሳተፈ መልኩ በቅንጅት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ከተማን የማልማት እና ምቹ የመኖሪያ ከተማ የማድረጉ ሂደት በዋነኛነት ባለሀብቱን እና ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በቅንጅት እየተካሄደ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ህዝባዊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ በአራዳ ክፍለ ከተማም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) እና የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በተገኙበት ህዝባዊ መድረኩ ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ መክፈቻ ላይ ባለፈው አመት ከተካሄዱ የህዝብ ውይይቶች በኋላ ከነዋሪው ለተነሱ ጥያቄዎች የተሰጡ ምላሾች፣ የከተማ አስተዳደሩ ህዝብን ባሳተፈ መልኩ እያከናወናቸው ያሉ የልማት ስራዎች እና የመጡ ለውጦችን እንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ እንደሀገርም በኢኮኖሚ፣ በማህባራዊ እና ፖለቲካ የተከናወኑ ተግባራትን እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን የተመለከተ ገለጻ ተደርጓል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በሀገር ደረጃ እና በአዲስ አበባ ከተማ የመጡ ለውጦች የሚደነቁ እና ተጨባጭ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች ሊፈቱ ይገባቸዋል ያሏቸውን ጥያቄዎች እና አስተያየቶችም አንስተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመድረኩ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን ከተማዋን የማልማት እና ምቹ የመኖሪያ ከተማ የማድረጉ ሂደት በዋነኛነት የግል ባለሀብቱን እና ነዋሪውን ባሳተፈ መልኩ በቅንጅት እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች በአብዛኛው ታቅደው በስራ የሚመለሱ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ናቸው።
በቀጣይም በግብርና እና በኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነት ላይ እየተመዘገበ ያለውን ስኬት አጠናክሮ ማስቀጠል ዋነኛው መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ ስኬታማ የልማት ተግባራትን በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች የማስፋት ስራ በስፋት መከናወኑን ተናግረዋል።
ህዝባዊ ውይይቱ በቀጣይነትም በወረዳ እና በብሎክ ደረጃ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡