ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ የልማት ስኬቶች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የከተማዋን ዕድገትና ገጽታ የገለጡ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ የመዲናዋ የልማት ስኬቶች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የከተማዋን ዕድገትና ገጽታ የገለጡ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ3ኛ ዙር ሰልጣኝ አመራሮች ገለጹ፡፡

''በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እመርታ'' ሶስተኛ ዙር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰልጣኝ አመራሮች በመዲናዋ የተከናወኑና በግንባታ ላይ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት የኢንስፔክስንና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሃይለየሱስ ባልከው፤ በአዲስ አበባ የተገኙ የልማት ስኬቶች መንግስት ለህዝብ የገባውን ቃል ምላሽ የሰጠበት ነው ብለዋል።

በዚህም የአዲስ አበባ የልማት ስኬቶች አዳዲስ የመዝናኛ፣ የመንገድ፣ የትራፊክ ማሳለጫና ሌሎች የመሰረተ ልማት ተግባራት መዲናዋን በሁሉም ዘርፍ በማዘመን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እያደረጋት መሆኑን ገልጸዋል።

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት አፈ-ጉበዔ ብዟየሁ ገሰሰ በበኩላቸው፤ የመደመር መንግስት እሳቤ የአዲስ አበባን ዕድገትና ገጽታ በተግባር መግለጡን ተናግረዋል።

በቀጣይም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት የፋይናንስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ላግ ቲኮ በበኩላቸው፤ የቆሻሻ መጣያ የነበሩ ስፍራዎች አሁን ላይ የመዝናኛና የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን በቅተዋል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የተገነቡ በሂደት ላይ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን የሥራ ዕድል ፈጠራና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቤዛዊት ጌታቸው፤ በወንዝ ዳር፣ በመንገድ፣ በመዝናኛ ስፍራና በመኖሪያ ቤት ግንባታ ላይ የተሰሩ ስራዎች አስደናቂ ናቸው ብለዋል፡፡

በመዲናዋ የተሰሩ ስራዎች ሁሉ ሰው ተኮር መሆናቸውን ተመልክቻለው ያሉት ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት የሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ ብሩክ መንግስቱ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም