ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝብ እና የመንግስት ቅንጅት ውጤት ናቸው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝብ እና የመንግስት ቅንጅት ውጤት መሆናቸውን በየካ ክፍለ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ውይይት ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች "የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች" በሚል ሀሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰሩ ያሉ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝብ እና የመንግስት ቅንጅት ውጤት መሆናቸውን በየካ ክፍለ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ውይይት የተሳተፉ የህበረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል።


 

ነዋሪዎቹ ሀገርን የማበልፀግ ርዕይ የሚጨበጥ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ በመድረኩ ላይ እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች የለውጡ መንግስት የህዝብ ኃብትን በተገቢው መንገድ በመጠቀም የልማት ስራዎችን በፍጥነት እና በጥራት ማከናወን በመቻሉ የመጣ ስኬት ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ለዘመናት ያልተሰሩ ውዝፍ ስራዎችን በሁሉም ዘርፍ ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው ከተሞችን ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት የነዋሪው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በጉባ ብስራቶች ይፋ ያደረገቻቸው ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ሀገርን የማበልፀግ ርዕይን እውን እንደሚያደርጉ ያብራሩት ደግሞ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) ናቸው።

በየካ ክፍለ ከተማ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በተደረገው ዉይይት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም