ቀጥታ፡

በክልሉ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአስተሳሰብ ግንባታ ላይ በትኩረት ይሰራል

ደብረብርሃን፤ ህዳር 27 /2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአስተሳሰብ ግንባታ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አመለከተ።

"የዳበረ የወጣቶች ተሳትፎ  ለዘላቂ ልማት"  በሚል መሪ ሀሳብ የአፍሪካ ወጣቶች ቀን ክልላዊ ማጠቃለያ በደብረ ብርሃን ከተማ በፓናል ውይይት ተካሄዷል። 


 

የክልሉ ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ  ዘላለም አረጋ እንደገለፁት፤ በክልሉ እየተከናወኑ በሚገኙ ሁለንተናዊ የልማት ተግባራት የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው። 

በተለይ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአስተሳሰብ ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው ብለዋል። 

በክልሉ የወጣቶችን የውሳኔ ሰጪነት ሚና የማሳደግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል። 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ገጠር ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው ወጣቶች በተደራጀ አግባብ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የክልሉ መንግስት እየሰራ ነው ብለዋል። 


 

በክልሉ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተዘጋጀው የ25 ዓመት አሻጋሪ እቅድ የወጣቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። 

እንዲሁም ወጣቶች የክልሉን ሰላም በዘላቂነት የማረጋገጥ ሚናቸውን በማሳደግ ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 

የደብረ ብርሃን ከተማ  አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንዳሉት የወጣቶችን ተሳትፎ ማሳደግ  በተለይ ለከተማ ልማት እድገት የማይተካ ሚና እንዳለው አመልክተዋል። 

የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበራት ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ግርማ አቸነፍ  እንዳሉት ወጣቶች በተደራጀ አግባብ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም