በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የህዝብን ተሳትፎ ማሳደግ ለፖለቲካ ባህል ግንባታ መሰረት የሚጥል ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የህዝብን ተሳትፎ ማሳደግ ለፖለቲካ ባህል ግንባታ መሰረት የሚጥል ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የህዝብን ተሳትፎ ማሳደግ ለፖለቲካ ባህል ግንባታ መሰረት የሚጥል መሆኑ ተገለጸ።
''የጉባ ብስራቶች፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ ጃንጥራር አባይ ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ ለመድረኩ ባቀረቡት የመነሻ ሃሳብ፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአዲስ አበባ ሰው ተኮርና ግዙፍ የልማት ስኬቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
በመደመር መንግስት የተፈጸሙ አስደናቂ የልማት ስኬቶችም የመዲናዋንና የኢትዮጵያን ብልጽግና መፃኢ ዕድል የተሻለ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የኮሪደር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነት ቅነሳና የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ መርሃ ግብሮች መዲናዋን የሚመጥን ውጤታማ ስራ መሰራቱን አስረድተዋል።
በመዲናዋ ነዋሪዎች የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስኬቶችን ህዝብን ባሳተፈ አሰራር ቀጣይነት ላለው ዕድገት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በመዲናዋ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሕዝባዊ ውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአዲስ አበባ ብሎም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የመልማት ፍላጎት የሚያሳኩ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በክፍለ ከተማው የመንገድ መሰረተ ልማትን ጨምሮ የህዝብን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ የሰጡ የልማት ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የውሃ፣ የመብራት፣ የገበያ ማረጋጋት፣ የትውልድ ግንባታና የአገልግሎት አሰጣጥ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፤ የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ልዕልና ለማረጋገጥ እንደሚተጋ የሕዳሴ ግድብ ስኬትና የጉባ ብስራት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ማሳያ ናቸው ብለዋል።
በቀጣይም ህዝብ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የኢንዱስትሪ ማዕከል የሆነችው የአቃቂ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ያነሷቸው የመብራት፣ የውሃ አቅርቦትና ፍሳሽ አወጋገድ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፤ የመደመር መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከህዝብ ጋር በቅርበትና በትብብር የሚሰራ መንግስት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በዜጎች ቁርጠኛ ተሳትፎ በተለያዩ ዘርፎች የሀገርን ዕድገት የሚያሳልጡ እመርታዊ ስኬቶች እየተመዘገበ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መንግስት ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በማዳመጥ በየጊዜው ምላሽ ለመስጠት እያደረገ ያለው ጥረትን አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት መሰረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል።
አገር የምትገነባው በተባበረ ክንድ እንደመሆኑ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ተሳትፎና አሻራ ለተሻለ አገር ግንባታ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞም መንግስት በየዓመቱ በሚሊዮን ለሚልቁ ዜጎች በተለያዩ አማራጮች የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ካለፍ ፍላጎት አኳያ ቀጣይነት ያለው ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።