ቀጥታ፡

የሀገርን ብልጽግና የሚያሳልጥ ችግር ፈቺ የፈጠራ አቅም እየጎለበተ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ የሚያሳልጥ ችግር ፈቺ የፈጠራ አቅም እየጎለበተ መምጣቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩትና በኤስ.ኤን.ቪ ዓለም አቀፍ ድርጅት ትብብር ለ10 ቀናት የተካሄደው 6ኛው ሀገር አቀፍ ''ብሩህ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር'' ተጠናቋል።


 

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ፤ በውድድሩ ከተሳተፉ 251 የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ተወዳዳሪዎች ውስጥ አንድ መቶ የሚሆኑት ለሽልማት በቅተዋል ብለዋል።

''ማሰልጠን፣ መሸለምና ማብቃት” የሚል መሪ ሃሳብ በተሰጠው ብሩህ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር የግብርና፣ ጤና፣ ቴክኖሎጂና ሌሎች ዘርፎች ምርታማነትን የሚያሻሽሉ የፈጠራ ስራዎች መቅረባቸውን ገልጸዋል።

አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችንም በመረጃ ቋት በማደራጀት በኢንተርፕርነርሽፕ ስታርት አፕ ፈጠራ የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት እያሳደገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ የሚያሳልጥ ችግር ፈቺ የፈጠራ አቅም እየጎለበተ ነው ያሉት አቶ ሰለሞን፤ በፈጠራና ፍጥነት በዕውቀትና ክህሎት የበለጸጉ ዜጎችን የማፍራት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሀሰን ሁሴን (ዶ/ር)፤ ብሩህ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር የኢትዮጵያዊንን ዕምቅ የፈጠራ ክህሎት በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያዊያን የፈጠራ ክህሎት ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና አጋዥ የሚሆንበትን የማበረታቻ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የፈጠራ ባለሙያዎችም የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በትጋት በማለፍ ለበለጠ ውጤት እንዲበቁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቦሩ ካና በበኩላቸው፤ ብሩህ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር ውጤታማ ስታርት አፖችን ማፍራት እያስቻለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በኤስ.ኤን.ቪ ዓለም አቀፍ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጁሊ ግርሃም፤ በውድድሩ የተመረጡ የፈጠራ ስራዎች ወደ ስራ እንዲገቡ በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የፈጠራ ስራዎች ለኢትዮጵያ እድገት ማዕከል ሆነው እንዲቀጥሉ በትብብር እንሰራለን ብለዋል።

በፈጠራ ውድድሩ በግብርና ፣ በጤና ፣ በቴክኖሎጂና ሌሎች ዘርፎችን የሚደግፉ የፈጠራ ስራዎች ተሸላሚ ሆነዋል።

ከእነዚህም መካከል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የፈጠራ ባለሙያዎች የፈጠራ ስራቸው ለተኪ ምርት፣ ለግብርና ምርት ጥራት እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች ባማከለ መልኩ የሚኖረውን ጠቀሜታ ገልጸዋል።

በቀጣይም የፈጠራ ስራቸውን በስፋት ወደ ገበያ ለማስገባትና የስራ ዕድልን ለማስፋፋት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም