የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በድምቀት ለማክበር የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በድምቀት ለማክበር የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)
ሆሳዕና፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በድምቀት ማክበር የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት መደረጉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለፁ፡፡
20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በመጪው ሰኞ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በሆሳዕና ከተማ ለሚከበረው በዓል የተደረጉ ዝግጅቶችን አስመልክተው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም በመጪው ሰኞ በክልሉ የሚከበረውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በደመቀ መልኩ ለማክበር የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ የክልሉ ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹና ውብ እንዲሆኑ የኮሪደር ልማትና ሌሎች የመሰረተ ልማት ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
በዓሉን በድምቀት ለማክበር በሁለንትናዊ መልኩ ሲደረጉ የነበሩ ዝግጅቶች በአሁኑ ወቅት በተሟላ መልኩ ተጠናቀው ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ እንግዶችን እየተቀበሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በዓሉ ቀደም ሲል በክልሉ ባሉ ሁሉም መዋቅሮች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ ሲከበር መቆየቱንም አመልክተዋል፡፡
በዚህም በክልሉ ህዝቦች መካከል የጋራ ትርክትን ለመገንባትና የእርስ በርስ ትስስር እንዲጠናከር ከማድረግ ባለፈ የኢትዮጵያዊነት እሴት እንዲጎለብት ተሰርቷል ብለዋል፡፡
የቀኑ መከበር የጋራ ትርክትን ለመገንባት ካለው ፋይዳ በተጨማሪ የክልሉን ሰላምና የልማት ሥራዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል የጎላ እገዛ እንዳለውም ገልጸዋል።
በነገው እለትም በፌዴራሊዝም ዕንሰ ሀሳብ ላይ ምክክር እንደሚደረግ ገልጸው፣ በመድረኩ የሚነሱ ሀሳቦችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ የማድረግ ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት።
በበዓሉ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጪ ዜጎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል፡፡