የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለመጉዳት የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ከመንግስት ጋር በመሆን እንታገላለን - የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለመጉዳት የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ከመንግስት ጋር በመሆን እንታገላለን - የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት
አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለመጉዳት የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ከመንግስት ጋር በመሆን እንደሚታገል የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) ገለጸ።
የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) አመራር አባላት ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር ባደረጉት ዘላቂ የሰላም ስምምነት ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኢትዮጵያን የትርምስ ቀጣና ለማድረግ ጠላት ከውጭም ከውስጥም እያካሄደ ያለው ሴራ እንደማይሳካም የአመራር አባላቱ ጠቁመዋል።
የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሃላፊ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ በክልሉ በተከሰተው ግጭት ህዝቡ ያልተገባ መስዋዕትነት ሲከፍል ቆይቷል።
ይህ እንዲያበቃ ድርጅቱ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር ዘላቂ የሰላም ስምምነት ማድረጉን አስታውሰው፤ በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እንዲሁም ለህዝቡ ተጠቃሚነት በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱን አብራርተዋል።
በማረሚያ ቤት ያሉና የገንጣይ አስገንጣይ አጀንዳ የማይከተሉ የፋኖ አባላት ከእስር እንዲፈቱ፣ የአካል ጉዳትና ሌሎች ጉዳቶች የደረሰባቸው መልሰው እንዲቋቋሙ ስምምነት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።
አቅምና ችሎታ ያላቸው የፋኖ አባላት ወደነበሩበት የስራ መዋቅር ተመልሰው እንዲሰሩ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን የትርምስ ቀጣና ለማድረግ ጠላት ከውጭም ከውስጥም እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ከመንግስት ጋር በመተባበር ይህ ሴራ እንዳይሳካ እናደርጋለን፤ ለአገራችን ብሄራዊ ጥቅምም እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የመረጃና ደህንነት ሃላፊ መስፍን አባተ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የፋኖን ትግል ለመቀማት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል ።
የውጭ ጠላቶችን ሴራ መገንዘብ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ድርጅቱ ወደ ስምምነቱ የመጣው ይህ የውጭ ሃይሎች ሴራ እንዳይሳካ ለማድረግም ጭምር ነው ብለዋል።
ከአማራ ክልል መንግስት ጋር በተደረገው ድርድር የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ ስምምነት መደረሱን አብራርተዋል።
የፌዴራል መንግሥትና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡና ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል።
በዚህም ጥረት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) መካከል ዘላቂ ሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወቃል።