ቀጥታ፡

የመደመር መንግስት ለዜጎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ የመደመር መንግስት ለዜጎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ሥራዎችን እንደሚገነባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ ከተማን የሚመጥን አስደናቂ የልማት ስኬት መምጣቱን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሕዝባዊ መድረክ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

''የጉባ ብስራቶች፣ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ እና የመድረኩ ተሳታፊዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያን የዘመናት የብልጽግና መሻት የሚያረጋግጡ ተጨባጭ የልማት ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

ሀገራዊ ለውጥ የወለደው የብልጽግና መንግስትም አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሁሉም ዘርፎች ዕድገትን የሚያስቀጥል ልማት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ባቀረቡት መነሻ ጽሁፍ፤ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ለመዲናዋ ነዋሪዎች የልማት ጥያቄ መልስ የሰጡ የልማት ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የመዲናዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተገባው ቃል መሰረትም ከግዙፍ እስከ መካከለኛ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የአዲስ አበባን የመልማት አቅም የገለጡ ስኬቶች መምጣታቸውን ተናግረዋል።

የገበያ ማዕከላትን በመገንባት እንዲሁም የእሁድና ቅዳሜ ገበያ ተደራሽነትን በማስፋት የመዲናዋን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና የሚያቃልልና ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኝበት ምቹ ምኅዳር መፈጠሩንም አስረድተዋል።

በመኖሪያ ቤት፣ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ፣ በቱሪዝምና ኢንዱስትሪ ዘርፍ የአዲስ አበባ ከተማን ውበት በማላበስ መዲናዋን የኢትዮጵያ ብልጽግና ተምሳሌት የሚያደርጉ ለውጦች መምጣታቸውን አንስተዋል።

በቀጣይም በመደመር መንግስት የብዝኅ ዘርፍ የልማት እሳቤ የመዲናዋን ነዋሪዎች የከተሜነት አኗኗር የሚያሻሽሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሕዝባዊ ውይይት የተሳተፉ የመዲናዋ ነዋሪዎችም፤ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት በአጭር ጊዜ አዲስ አበባን የሚመጥን አስደናቂ የልማት ስኬት መምጣቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም የመሠረተ ልማት ግንባታ አቅሞችንና የመልካም አስተዳደር ስኬቶችን በማስፋት የኑሮ ውድነት ጫናን የሚያቃልሉ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።


 

የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ በመድረኩ ማጠቃለያ እንደገለጹት፤ መንግስት ህዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።

ለአብነትም የመንግስትን የሰላም አማራጭ የተቀበሉ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች የኢትዮጵያ የልማት አካል እየሆኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በቀጣይም የሰላም አማራጭ የሚከተሉ አካላትን ለመቀበል በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)፤ መንግስት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ትርጉም ባለው መልኩ መለወጥ የሚያስችል የልማት ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ተረጂነትን ለማስቀረት የ30 ቢሊየን ዶላር የጉባ ብስራት ግዙፍ የልማት ውጥኖች ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የመደመር መንግሥት ዜጎች የሚያነሷቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ስኬቶችን እንደሚያሰፋ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም