መንግስት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት የህብረተሰቡን ጥያቄዎች በማዳመጥ ምላሽ እየሰጠና ሀሳቦቹን በእቅድ በማካተት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በህዝባዊ ውይይት መድረክ ላይ ገለጹ።
የውይይት ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ መንግስት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል።
በአዲስ አበባ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች "የጉባ ብስራቶች፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
በኮልፌ ቀራንዮ በተካሄደው የውይይት መድረክ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሀይ ጳውሎስ፣ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ኃላፊ ሊድያ ግርማ እንዲሁም ሌሎች የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እና የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ሀላፊ ሊድያ ግርማ ከዚህ ቀደም ከህብረተሰቡ በተነሱ ጥያቄዎች ላይ የተሰጡ ምላሾችን እና ቀጣይ የልማት ስራዎች ላይ ገለጻ አድርገዋል።
በገለጻቸውም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት መንግስት የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻሉን፣ የተቋማት ሪፎርም እና ዲጂታል አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረጉን ጠቁመው፤ በዚህም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሲስተዋሉ የቆዩ ብልሹ አሰራሮችን እየቀረፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመፍታትም የምርት አቅርቦት እንዲሻሻል መደረጉን እና በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ውጤታማ ስራ መሰራቱን ጠቁመው፤ መንግስት እያከናወናቸው የሚገኙ የልማት ስራዎች በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም በርካታ የልማት ስራዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ከነዚህም መካከል ብሔራዊ ፕሮጀክቶች የሆኑት የጉባ ብስራቶችን ጠቅሰዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መንግስት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን አድንቀው፤ ይህንን ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ሀገራዊ ትልልቅ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በተማሪዎች ምገባ ላይ የተጀመረው ስራ እንዲጠናከርና የጤና ተቋማት ግንባታ እንዲስፋፋ ጠይቀው፤ በተጨማሪም የኑሮ ውድነትን ለመፍታት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ይበልጥ ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።
ከመሰረተ ልማት እንዲሁም ከውሃ እና ከኤሌትሪክ ኃይል መቆራረጥ ጋር ያሉ ተግዳሮቶች እንዲፈቱላቸውም ጠይቀዋል።
በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሀላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምጸሀይ ጳውሎስ፤ መድረኩ ለበለጠ መግባባት እና ስራ ይጠቅማል ብለዋል።
አሁንም የላቀ ስኬት ለማሳካት በጋራ በህብረት መቆም እንደሚገባ አስገንዝበው፤ የመንግስት ትልቁ እይታው ህብረተሰቡን አዳምጦና የፍላጎቶቹን ጥያቄዎች በእቅድ አካቶ ምላሽ እየሰጠ ወደፊት እንደሚሄድ ተናግረዋል።
መንግስት በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በቱሪዝም እንዲሁም በዲጂታላይዜሽን ላይ በርካታ ኢኒሼቲቮች ቀርጾ ተግባራዊ ማድረጉን ገልጸው፤ ይህም በርካታ ውጤቶች እንደተመዘገበበት ገልጸዋል።
ከፊት ለፊታችን ለሚጠብቁን ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ በውይይቱ የተነሱ ሀሳቦች ተይዘው በየደረጃው እንደሚፈቱም አረጋግጠዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ በበኩላቸው፤ ህዝብን በማሳተፍ እንዲሁም ልማትን ብሔራዊ አጀንዳ በማድረግ በርካታ ድሎች መገኘታቸውን ጠቁመው፤ ለልማት ስራዎች የህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን በየደረጃው ለመፍታት መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዓይናለም፤ የህዝብን አንድነት እና አብሮነት ሊሸረሽሩ የሚሰሩ አካላትን መታገል እንደሚገባ ነው አጽንኦት የሰጡት።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ሀላፊ ሊድያ ግርማ በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ የውሀ ተደራሽነትን ለማሳደግ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን እና የስራ እድል ፈጠራ የርብርብ ማዕከል ሆኖ መቀጠሉን አስታውቀዋል።
በቀጣይም የዜጎችን ጥያቄ በትብብር የመፍታት ስራዎች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።