ቀጥታ፡

ማዕከሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ምርጥ ዘርን በጥራትና በፍጥነት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ ነው

አሰላ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ የቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ምርጥ ዘርን በጥራትና በፍጥነት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

የምርምር ማዕከሉ ከጂአይዜድ ጋር በመተባበር ያስገነባው ዘመናዊ የዘር ማበጠሪያ ማሽን ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት ጀምሯል።

የቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ አለማየሁ እንዳሉት ማበጠሪያ ማሽኑ ማዕከሉ የሚያባዛውን መስራች ዘር በጥራትና በፍጥነት አርሶ አደር ዘንድ ለማድረስ ቁልፍ ሚና ያለው ነው ብለዋል።

ዘመናዊ የምርጥ ዘር ማበጠሪያ ማሽኑ ምርትና ምርታማነት ለመጨመር እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማሳካትም ትልቅ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

ማበጠሪያ ማሽኑ በቀን እስከ 2 ሺህ ኩንታል ዘር የማበጠር አቅም ያለው ሲሆን ማሽኑ ከማዕከሉ ባለፈ በምርጥ ዘር ብዜት ለተሰማሩ የአካባቢው አርሶ አደሮች፣ ማህበራትና ባለሃብቶች ጭምር በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ማሽኑ ዘር ከማበጠር እስከ ማሸግ ድረስ ያለውን ሂደት በማከናወን የምርጥ ዘርን ጥራት በከፍተኛ ደረጃ የሚያስጠብቅ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተወካይና የምርምር ጥራት ማረጋገጫና ግምገማ ዳይሬክተር በድሩ በሽር (ዶ/ር) እንደገለፁት የቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ዛሬ ወደ ስራ ያስገባው ማሽን አገሪቷ የያዘችውን ምርታማነት የማሳደግ እቅድ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ ነው።

በተለይ የስንዴና ሌሎች ሰብሎች ምርጥ ዘር በወቅቱ ለአርሶ አደሮች ለማድረስ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በየማዕከላቱ በምርምር የሚወጣውን ምርጥ ዘር በጥራትና በፍጥነት አርሶ አደሩ ዘንድ ለማድረስ ያለውን የማበጠሪያ ማሽን ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል ።

በኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ሙስጠፋ ሁሴን በበኩላቸው የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግም ሆነ የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ጥራት ያለው ምርጥ ዘር አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ማሽኑ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ በክልሉ የነበረውን የምርጥ ዘር ጥራት ችግር የሚቀንስ መሆኑን ጠቅሰው በክልሉ በምርጥ ዘር ብዜት ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ትልቅ እድል ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የምርጥ ዘር ዘርፍ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘነበ ወልደስላሴ እንደገለፁት ማሽኑ መነሻ ዘሮችን በወቅቱ አበጥሮ ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ጠቀሜታው የላቀ ነው።

''ከዚህ በፊት የዘር ማበጠሪያ ማሽን እጥረትና ችግር ነበረብን'' ያሉት አቶ ዘነበ ማዕከሉ ለአገልግሎት ያበቃው ለኮርፖሬሽኑ ስራ መሳካትም ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም