ቀጥታ፡

በከተማው የትምህርት መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በተደረገ ጥረት ውጤት ተገኝቷል

ዲላ ፤ህዳር 27/2018 (ኢዜአ)፡- በዲላ ከተማ የትምህርት መሰረተ ልማትን በማስፋት የተማሪዎች ውጤትን ለማሻሻል በተደረገ ጥረት ውጤት መገኝቱን የከተማው አስተዳደር ገለጸ።


 

በዲላ ከተማ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  የተገነቡ መማሪያ ክፍሎች ተመርቀው ለአገልግሎት በቁ።

የዲላ ከተማ አስተደደር ከንቲባ  መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት በከተማው የትምህርት መሰረተ ልማትን በማስፋት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በተደረገ ጥረት ውጤት ተገኝቷል።


 


በተለይ ህብረተሰቡን፣ የግል ባለሃብቱንና ባለድርሸ አካላትን በማስተባበር ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገ ጥረት የመማሪያ ክፍሎችን መገንባት ተችሏል ብለዋል፡፡

በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ዛሬ ለአገልግሎት የበቃው የመማሪያ ክፍል ምቹ የትምህርት ከባቢን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት የሚያጠናክር መሆኑንም አስረድተዋል።

በከተማው በህብረተሰብና በመንግስት ትብብር ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ 56 የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ያነሱት ደግሞ የከተማው ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ሆርዶፋ ናቸው።


 

በዚህም በክልላዊና ሀገራዊ ፈተናዎች የማለፍ ምጣኔ መሻሻል መቻሉን ጠቅሰው ተግባሩን በማጠናከር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።

የሀላል ወጣቶች በጎ አድራጎት ማህበር ሰብሳቢ አቶ ቶፊቅ ተማም በበኩሉ ማህበሩ ከ1 ሺህ 200 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች በቋሚነት የመማሪያ ግብዓቶች ሲደግፍ መቆየቱን ገልጿል።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ግለሰቦችን በማስተባበር በዲላ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያስገነባቸውን አራት የመማሪያ ክፍሎች ዛሬ አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉንም ተናግሯል።

ይህም በእውቀትና ስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመገንባት ወሳኝ በመሆኑ በትምህርት ዘርፍ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩም ገልጿል።

የዲላ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  ተማሪ አማኑኤል ኤፍሬም በበኩሉ ከዚህ ቀደም የነበረው የመማሪያ ክፍል ከእንጨትና ጭቃ የተሰራና የቆየ በመሆኑ ለመማር ይቸገሩ እንደነበር ገልጿል።

አዲሱ መማሪያ ክፍል ምቹ የትምህርት ሁኔታ እንዲኖር የሚያስችል በመሆኑ ጠንክሮ ለመማር የሚያስችል ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም