ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል አብሮነትን በማላቅ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ያጠናክራል

ሰመራ፣ህዳር 27/2018(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል አብሮነትን በማላቅ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን እንደሚያጠናክር የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ።

20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ''ዴሞክራሲያዊ  መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ተከብሯል። 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እንደገለፁት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል አብሮነትን በማላቅ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ያጠናክራል።

ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡና በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት ተማሪዎች አብሮነታቸውን በማጠናከር በዓሉን በጋራ ለማክበር መቻላቸውን ተናግረዋል።

ከኦሮሚያ ክልል የመጣችው ተማሪ አበባ ኦላኔ በዓሉን በጋራ ማክበራችን አብሮነታችንንና ትስስራችንን አጠናክሮልናል ብላለች።

ልዩነታችን ውበታችንና መገለጫችን በመሆኑ አንድነታችንን ከማጠናከር አላገደንም፤ ሊያግደንም አይችልም ስትልም አክላለች።

ከአፋር ክልል ፈንቲ ረሱ ዞን የመጣው ተማሪ ቢኒአሚን ሁሴን በበኩሉ በዓሉን ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር መልካም አጋጣሚን በመፍጠሩ በደስታ እናከብረዋለን ብሏል። 

በዓሉ አንድነታችንን አጠንክረን አንድ ላይ በማክበራችን አብሮነታችን እንዲልቅ ከማድረጉም ባለፈ መተሳሰባችን እንዲጨምር አድርጓል ያለው ደግሞ ከደሴ ከተማ የመጣው ተማሪ መሐመድ የሱፍ ነው። 

ከኦሮሚያ ክልል ነጆ ከተማ የመጣው ተማሪ ዋቅቶላ ታሲሳ በበኩሉ በዓሉ ባህልና ወጋችንን ጠብቀን በድምቀት የምናከብረው ብቻም ሳይሆን አንድነታችንን የምናጠናክርበት ነው ብሏል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም