ቀጥታ፡

በዓባይ ወንዝ ጉዳይ የግብጽ ጠቅልሎ የመያዝ የቅኝ ግዛት ትርክት በዓለም አቀፍ የውሃ ህግም ሆነ በሌሎች መመዘኛዎች ተቀባይነት የሌለው ነው

አርባ ምንጭ፤ ህዳር 27/2018 (ኢዜአ)፡- በዓባይ ወንዝ ጉዳይ የግብጽ ጠቅልሎ የመያዝ የቅኝ ግዛት ትርክት በዓለም አቀፍ የውሃ ህግም ሆነ በሌሎች መመዘኛዎች ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን ገለጹ።

የዓለም ታላቁ ወንዝ ለሆነውን ዓባይ ከ86 በመቶ በላይ የውሃ መጠን የምታበረክተው የጥቁር ዓባይ መነሻ ኢትዮጵያ መሆኗ የማይካድ እውነታ ነው።

በዚህ ወንዝ ላይ ከእኔ በላይ ሊወስን ብሎም ሊጠቀም የሚችል ሀገር መኖር የለበትም የሚለው የግብጽ የቅኝ ግዛት አቋምና የተሳሳተ ትርክት አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ዓባይ የተፋሰሱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ በፍትሃዊነት የመጠቀም አቋም በመያዝ እየሰራች መሆኑን ዓለም የሚገነዘበው ሀቅ ነው።

የግብጽን የተሳሳተ አቋምና የኢትዮጵያን በፍትሃዊነት የመጠቀም ጥረት በተመለከተ ኢዜአ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምሁራንን አነጋግሯል።

በዩኒቨርሲቲው የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምሩ ተሰማ(ዶ/ር) ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት የያዘችው የተሳሳተ ትርክት ለዚህ ዘመን የማይመጥንና ሊነሳ የማይገባው አጀንዳ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የተፋሰሱን ሀገራት በማይጎዳ መልኩ ወንዙን የማልማትና የመጠቀም መብቷን የሚከለክላት እንደሌለ እየታወቀ የበይ ተመልካች ሆና እንድትኖር የግብጽ ፍላጎት መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዳይሳካ ከዓለም አቀፍ የውሃ አጠቃቀም ህግ በተቃርኖ በመቆም ብዙ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን ስታደርግ ብትቆይም በኢትዮጵያውያን ብርቱ ጥረት ግድቡ ለስኬት መብቃቱን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከግድቡ መጠናቀቅ በኋላም ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን ማድረጓን እንደቀጠለች ያነሱት ኢንጂነር ታምሩ(ዶ/ር)፣ ድርጊቷ የሚወገዝና በፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ውሃ አጠቃቀም ህግ መሰረት ምክንያታዊ፣ ፍትሃዊና የታችኞቹን የተፋሰሱን ሀገራት በጉልህ በማይጎዳ መልኩ የመጠቀም መብት መኖሩን አንስተው የግብጽ ዓላማ ግን ከእኔ ውጭ ሌላው አይጠቀም የሚል ፍፁም ግለኝነት የሚታይበት መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም በዓባይ ጉዳይ የግብጽ ጠቅልሎ የመያዝ የቅኝ ግዛት ትርክት በዓለም አቀፍ የውሃ ህግም ሆነ በሌሎች መመዘኛዎች ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

የግብፅ ግትር አቋም ኢትዮጵያ አንጡራ ሀብቷን አልምታ የመጠቀም መብቷን የሚጋፋ ቢሆንም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የውሃ አጠቃቀም ህግ መርህ ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ አካሄድ እየተከተለች መሆኑን አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የውሃ ሀብት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ኤልያስ ገበየሁ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ግብፅ ከዓባይ ወንዝና ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የምታራምደው ግትር አቋም እና የቅኝ ግዛት እሳቤ በዚህ ዘመን ሊነሳ የማይገባውና ጊዜው ያለፈበት መሆኑን ተናግረዋል።

በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮችን በመግፋት የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብን ለማራመድ በግብጽ መንግስት ባለስልጣናት የሚደረገው ተደጋጋሚ እንቅስቃሴ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን እውነታ ጋር የማይሄድ መሆኑን የኢፌደሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጹ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም