በክልሉ ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት የቱሪስት ፍሰትን በመጨመር ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋፅኦ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት የቱሪስት ፍሰትን በመጨመር ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋፅኦ እያደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት የቱሪስት ፍሰትን በመጨመር ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው አመራርና ሠራተኞች፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ ባለድርሻ አካላት የዓለም ቱሪዝም ቀን አስመልክቶ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክንና በፓርኩ የተሰሩ መሰረተ ልማቶችን ጉብኝተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሰለሞን ታምሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት የተለያዩ መዳረሻ ስፍራዎች በመገንባትና ነባሮችን በማስተዋወቅ ለኢኮኖሚ ምጭነት እንዲውሉ በትኩረት እየተሰራ ነው።
ዘርፉ ከገቢ ምንጭነት ባሻገር የክልሉንና የሀገርን በጎ ገጽታ ከመገንባት አኳያ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑንም ነው ያመላከቱት።
እየተሰሩ ያሉት ሥራዎች በክልሉ የሚገኙ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም መዳረሻዎችን አሟጦ መጠቀም የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ምትኬ ቢተውልኝ(ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ ወደ ቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች የተሰሩ መንገዶች፣ ሎጆችና ሌሎች አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች ፍሰቱ እንዲጨምር አስችለዋል ነው ያሉት።
ኮሚሽኑ በተለያዩ ቋንቋዎችና የማስታወቂያ ዘዴዎች በመጠቀም የክልሉን የቱሪስት መዳረሻዎች በስፋት እያስተዋወቀ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ ገረመው መብራቱ እንደተናገሩት፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት ፓርኩ በመሠረተ ልማት ችግር ምክንያት በቂ የቱሪስት ፍሰት እንዳልነበረው አስታውሰዋል።
በመንግሥት በተሰጠው ትኩረት እየተገነቡ ያሉት መሠረተ ልማቶች ችግሩን በመፍታት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው ይህም የፓርኩን የጎብኚዎች ቁጥር በማሳደግ ላይ ይገኛል ብለዋል።