ቀጥታ፡

በእውቀት የዳበረ ትውልድ ለመገንባት የተጀመረው ጥረት ይጠናከራል -ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬደዋ፣ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ በድሬደዋ አስተዳደር በእውቀት የዳበረ እና የተሟላ ስብእና ያለው ትውልድ ለመገንባት እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

በመደመር ትውልድ የመፅሐፍ ሽያጭ ለተገነባው እመርታ ዘመናዊ ቤተ-መፅሐፍ የመፅሐፍት ግብዓት የማሰባሰብ ስራ ዛሬ ተካሄዷል።


 

ዛሬ በተካሄደው የመፅሐፍ ግብዓት ማሰባሰብ ላይ የአብርሆት ቤተ-መፅሐፍት፣ የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ፣ ግለሰቦች እና ባለሃብቶች ከ30 ሺህ በላይ የተለያዩ መፅሐፍትን ለግሰዋል።

በዚሁ ጊዜ የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ትውልዱ በሁሉም መስክ የተሻለ እውቀት እና የተሟላ ስብእና እንዲኖረው ማንበብ አለበት ብለዋል።

በተለይም የቴክኖሎጂ ዘርፍ እየረቀቀ ባለበት በዚህ ዘመን የተሻለ እውቀት መታጠቅ እንደሚገባ ያመለከቱት ከንቲባው ለዚህ ደግሞ መሰረተ ልማት ማሟላት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

በመደመር ትውልድ የመፅሐፍ ሽያጭ በድሬደዋ የተገነባው ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍትም የተሻለ ትውልድ ለማፍራት ትልቅ እገዛ እንደሚያደረግ ገልጸዋል።

ቤተ መፅሐፍቱን ወደ ስራ ለማስገባት የመፅሐፍት ግብዓት የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው የተለያዩ አካላት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዛሬው እለትም ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው በውጭና በአገር ውስጥ የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆች እና ወዳጆች የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።


 

የአብርሆት ቤተ መፅሐፍት ምክትል ዳይሬክተር ሜሮን ደሳለኝ፣ እስካሁን ለቤተ መጽሐፍቱ ከተለገሰው መፅሐፍት ባሻገር ቤተ መፅሐፍቱ በሙሉ አቅሙ ስራ እንዲጀምር የቴክኖሎጂ እና የቴክኒክ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

ሦስት ሺህ መፅሐፍት የለገሰው የሐረማያ ዩኒቨርስቲ በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለፁት የዩኒቨርስቲው የቤተ-መፅሐፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ግርማ ብዙ ናቸው ።

የእመርታን ቤተ-መፅሐፍት የሚያስተዳድረው የድሬዳዋ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንደሰን አባይ በበኩላቸው ከመደመር ትውልድ መፅሀፍት ሽያጭ የተገነባው ዘመናዊ ቤተ-መፅሐፍት ወደ ስራ ለማስገባት የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የግብዓት ማሰባሰቡ ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም