ቀጥታ፡

መንግሥታችን ሕዝብን ያዳምጣል፣ ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ይሰጣል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥታችን ሕዝብን ያዳምጣል፣ ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ይሰጣል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ ዛሬ ከማለዳ አንስቶ ከነዋሪዎቻችን ጋር ሰፊ ውይይቶችን አካሂደናል ብለዋል።

ውይይቶቹ በመዲናችን አዲስ አበባ በሚገኙ በሁሉም ክፍለ-ከተሞች በስፋት ተካሂደዋል ነው ያሉት።


 

የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ባለሀብቶችና ምሁራንን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል ብለዋል።

የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋት በሚል ርዕስ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሕዝብ መድረኮች ላይ ከነዋሪዎቻችን ለተነሱ ጥያቄዎች፣ ቅሬታዎች እና አስተያየቶች በተግባር የተሰጡ ምላሾች፣ እንዲሁም ቀሪ ሥራዎችን አስመልክቶ በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል ሲሉም ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደራችን ከፍተኛ አመራሮችና ሚኒስትሮች መድረኮቹን በመምራት ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ የቤት ስራም ወስደዋል ነው ያሉት።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከተማችን በተለያዩ የልማት ሥራዎች አስደናቂ ስኬቶች የተመዘገቡት መንግሥትና ሕዝብ አንድ ሆነው በመቀናጀትና በመናበብ መፈጸም በመቻላቸው ነው ብለዋል።


 

ዛሬም በመንግሥትና በሕዝብ ትብብር የተሰሩ በርካታ ሥራዎችንና የተመዘገቡ ውጤቶችን ይበልጥ ለማጠናከር፣ እንዲሁም የሕዝብን ተሳትፎ ይበልጥ በሚያረጋግጡ ቀጣይ የጋራ ዕቅዶች ላይ እንደ ወትሮው ከነዋሪዎቻችን ጠቃሚ ግብዓት ያገኘንበት ፍሬያማ የውይይት መድረክ ነበር ሲሉም ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለነዋሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት ለሰጣችሁን ገንቢ አስተያየት፣ ለነበራችሁ ከፍተኛ ተሳትፎ፣ ለሰጣችሁን ውድ ጊዜ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ከልብ አመሰግናለሁ ብለዋል።

በቀጣይም ይበልጥ ተቀራርበን መሥራታችንን እንቀጥላለን ሲሉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም