በአምባሳደር ጀነራል ባጫ ደበሌ የተጻፈው የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ መጽሐፍ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
በአምባሳደር ጀነራል ባጫ ደበሌ የተጻፈው የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ መጽሐፍ ተመረቀ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦በአምባሳደር ጀነራል ባጫ ደበሌ የተጻፈው የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ መጽሐፍ ዛሬ ተመርቋል።
በምረቃው ላይም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ የተሰነደ የፀረ ሽምቅ ውጊያ ማኑዋል የነበራት ቢሆንም የተሻሻለ እንዳልነበረ አውስተው ''የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ" መፅሐፍ ግን ዘመኑን የሚመጥንና ለጦር መሪዎች ማስተማሪያነት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው ብለዋል።
አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ይህንን ጠቃሚ መጽሐፍ ለአንባቢያን በማበርከታቸው ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ከመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ብዙ የኛ ሀገር ጦር መሪዎች የሚፅፉት መፅሐፍ ታሪክ ላይ ያተኩራል፤ ''የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ" መፅሐፍ ግን ሳይንሳዊ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ይህንን በተግባር ያረጋገጡት ደግሞ ጄነራል ባጫ ናቸው ብለዋል።
በ187 ገፆች የተቀነበበውና በአምስት ምዕራፎች የተከፋፈለው ''የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ'' መፅሐፍ ስለሽምቅ ውጊያ ዳራና ልምድ የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የሸማቂና የአሸባሪ ቡድኖች ባህሪ የፀረ-ሽምቅ ውጊያና የፀረ-ሽምቅ ግብረ-ኃይል ዝግጅትን ምንነት የሚገልፅ ነው።