በጉራጌ ዞን የደረሱ ሰብሎችን በኮምባይነር በመታገዝ በፍጥነት የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጉራጌ ዞን የደረሱ ሰብሎችን በኮምባይነር በመታገዝ በፍጥነት የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ ነው
ወልቂጤ፤ ህዳር 26/2018(ኢዜአ):- በጉራጌ ዞን የደረሱ ሰብሎች ምርት ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይባክን በኮምባይነርና በደቦ እየሰበሰቡ መሆኑን አርሶ አደሮች ተናገሩ።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ በቸሃ ወረዳ የሸሬና ቆንደሬቼ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኑርሀሰን ለጋሽ በሶስት ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን ስንዴና ጤፍ በደቦ እየሰበሰቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ እየታየ ያለው እርጥበት የምርት መበላሸት እንዳያስከትል ሁሉም የአካባቢው ነዋሪ በመተጋገዝና በመቀናጀት ምርት ሳይባክን የመሰበሰቡን ስራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በወረዳው የቦራና ቱባ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ዚድኒ አህመዲን በ3 ነጥብ ሦስት ሄክታር ማሳ ላይ ያለሙትን ጤፍ በደቦ እየሰበሰቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በ5 ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን ጤፍና ስንዴ ምርት በኮምባይነር በመታገዝ በመሰብሰብ ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ በዞኑ በአበሽጌ ወረዳ የማመዴ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዳዊት አሰፋ ናቸው።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ፤ በዞኑ በመኸር እርሻ በተለያዩ ሰብሎች ከለማው ከ150 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ከ5 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል ።
በመኸር እርሻ ወቅት ከዚህ በፊት ያልተለመዱ ሩዝን ጨምሮ በቆሎ፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ጤፍና ስንዴ በኩታ ገጠም የእርሻ ስነ-ዘዴ መልማቱን ተናግረዋል።
በዞኑ በእርሻው ረገድ ያለውን አቅም በመጠቀምና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ሰብል ራስን የመቻልና ገቢ የማመንጨት ጥረት ውጤት እየታየበት እንደሆነ አስረድተዋል።
የደረሱ ሰብሎችን በህዝብ አደረጃጀት እንዲሁም በኮምባይነር በመታገዝ ያለብክነት የመሰብሰብ ስራ በተቀናጀ መንገድ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።