ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሊጉ ሁለተኛ ድሉን አስመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሊጉ ሁለተኛ ድሉን አስመዘገበ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 26/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2 ለ 1 አሸንፏል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አዲስ ግደይ በአራተኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ግብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪ መሆን ችሏል።
ጌትነት ተስፋይ በ65ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት እና ስምኦን ማሩ በ96ኛው ደቂቃም በጨዋታ ከመረብ ላይ ያሳረፏቸው ግቦች ወልዋሎን አሸናፊ አድርጓል።
ጋናዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋች ካሌብ አማንክዋ በመጀመሪያ አጋማሽ ማብቂያ በሁለት ቢጫ ካርዶች በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
በሊጉ ሁለተኛ ድሉን ያስመዘገበው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሰባት ነጥብ ደረጃውን ከ20ኛ ወደ 18ኛ ከፍ ቢያደርግም አሁን ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
በውድድር ዓመቱ ሶስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስምንት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል።