በአፋር ክልል አይሳኢታ ከተማ አቅራቢያ በመጠለያ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ጥሩ አያያዝ እየተደረገላቸው ነው - የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል አይሳኢታ ከተማ አቅራቢያ በመጠለያ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ጥሩ አያያዝ እየተደረገላቸው ነው - የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ
ሰመራ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል አይሳኢታ ከተማ አቅራቢያ በመጠለያ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ጥሩ አያያዝ እየተደረገላቸው መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው በስፍራው ተገኝቶ የስደተኞቹን አያያዝ ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነጎ(ዶ/ር)፤ በመጠለያ ካምፑ የሚገኙ ስደተኞች ጥሩ አያያዝ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በመጠለያው የጤና፣ የትምህርትና ሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በሌሎችም አገልግሎቶች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተጠቃሚ መሆናቸውን ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ መሀዲ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአይሳኢታ የስደተኞች ማዕከል በተለይም የአፋር ጎሳዎች የሆኑ ኤርትራዊያን በመጠለያው በብዛት እንዳሉ አንስተው፣ ስደተኞቹ በጥሩ አያያዝ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ስደተኞቹ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ከመላመድ ባለፈ በብዙ ማህበራዊ መስተጋብሮች ተሳስረውና የአገልግሎት ተጠቃሚ ሆነው እየኖሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
የስደተኞችና ተመላሽ አገልግሎት የሰመራ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኀላፊ አብዱረዛቅ ሙሳ፤ በክልሉ ከ61 ሺህ በላይ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞች ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለስደተኞቹ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።