ቀጥታ፡

በክልሉ የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ ነው

ደብረ ብርሃን፤ ህዳር 27/2018 (ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገለፁ።

"አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማህበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማህበራዊ እድገት " በሚል መሪ ሃሳብ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በደብረ ብርሃን ዛሬ ተከብሯል።


 

በመድረኩ የተገኙት ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የክልሉ መንግስት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች አካታች ማህበረሰብ ለመገንባት እየሰራ ነው።

በክልሉ በመደመር መንግስት እሳቤ የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም አካታች ማህበረሰብ ለመገንባት የአካል ጉዳተኞችን ህይወት በሚቀይሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም ገልፀዋል።


 

የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ንፁህ ሽፈራው እንዳሉት የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማቃለል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

በዚህም አካል ጉዳተኞች ሰርተው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ በንግድ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ የገቢ ማስገኛ ስራዎች እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የነበሩ ችግሮችን በማቃለል ፈጣንና ምቹ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መብቶች ማስከበር የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን የገለፁት ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ናቸው።

በከተማው በሚፈጠሩ የስራ ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው መደረጉን አንስተዋል።


 

የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍሬ ሰላም ዘገየ በበኩላቸው አሁን ላይ አካል ጉዳተኞች የመደራጀት መብቶቻቸው እየተከበረ መጥቷል ብለዋል።

በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፍ ተሰማርተው ተጠቃሚ የሆኑ በርካታ የአካል ጉዳተኞች እንዳሉም አረጋግጠዋል።

አሁንም የተሟላ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በየደረጃው ያለው አመራር ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

በመድረኩ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የአካል ጉዳተኞች ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም