በክልሉ በጸጥታ መዋቅሩ የተቀናጀ የህግ ማስከበር ሥራ ዘላቂ ሰላምና ልማትን የሚያረጋግጥ አስቻይ ሁኔታ ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በጸጥታ መዋቅሩ የተቀናጀ የህግ ማስከበር ሥራ ዘላቂ ሰላምና ልማትን የሚያረጋግጥ አስቻይ ሁኔታ ተፈጥሯል
ጎንደር፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በጸጥታ መዋቅሩ የተቀናጀ የህግ ማስከበር ሥራ በሁሉም አካባቢዎች ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ አስቻይ ሁኔታ መፈጠሩን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የጎንደር ከተማን ሰላም በማጠናከር ልማትን ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በየደረጃው ከሚገኙ የጸጥታ መዋቅር አመራሮች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ በሪሁን መንግስቴ እንደተናገሩት በክልሉ የህግ ማስከበር ሥራው ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ልማቱን ማስቀጠል የሚያስችል አውድ መፍጠር አስችሏል፡፡
የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ህግ የማስከበር አቅሙና ቁመናው በከፍተኛ ደረጃ አድጓል ያሉት አቶ በሪሁን ህብረተሰቡም የሰላሙ ባለቤት እራሱ መሆኑን በመገንዘብ የሚያደርገው ድጋፍና ተሳትፎ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል፡፡
የጸጥታ መዋቅሩ የህግ የማስከበር ተልዕኮውን በተናበበና በተቀናጀ መንገድ እየተወጣ መሆኑን ጠቁመው ክልሉ ወደ ተሟላ ሰላም እንዲሸጋገር ክፍተቶችን የማረም ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ(ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ አሁን ላይ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የጸጥታ መዋቅሩ ህብረተሰቡን በማሳተፍ እያደረገ ያለውን ጥረት ማጠናከር አለበት ብለዋል፡፡
ህዝቡ የሰላም አምባሳደር በመሆን የሚያከናውናቸውን የሰላም ግንባታ ተግባራት መደገፍ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ሰላምን መርጠው የመጡ የታጠቁ ሃይሎችም ሰላማዊ ህይወት እንዲመሩ መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኒራል መሰለ በለጠ፤ በበኩላቸው የፀጥታ መዋቅሩ በተናበበና በተቀናጀ መንገድ እያካሄደ ያለው የህግ ማስከበር ስራ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ መሰረት የጣለ ነው ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡና የጸጥታ መዋቅሩ ባከናወኑት የጋራ ጥረት የተገኘው ሰላም ለህዝቡ የልማት ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ናቸው፡፡
በመጪው ጥር ወር በታላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓት በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ለመታደም ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ እንዲቻልም ህዝቡና የፀጥታ መዋቅሩ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የከተማው የኮሪደር ልማት ስራ ለበዓሉ ድምቀት የሚፈጥር ነው ያሉት ቻላቸው በርካታ እንግዶችና ቱሪስቶች በዓሉን ለማክበር ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮማንደር አንተነህ ቴዎድሮስ፣ የከተማውን ሰላም ማጠናከርና የወንጀል ተግባራትን መቆጣጠር የሚያስችሉ 42 የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ ማዕከላትን መልሶ የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመድረኩ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን ጨምሮ በከተማው በየደረጃው የሚገኙ በጸጥታ ማስከበር ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት ተሳትፈዋል።