አርባ ምንጭና አካባቢዋን በቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
አርባ ምንጭና አካባቢዋን በቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አርባ ምንጭ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ አርባ ምንጭና አካባቢዋን በቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ከተማ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የማዕድን ሚኒስትር እና የገበታ ለሀገር አርባ ምንጭ ፕሮጀክት አስተባባሪ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ገለጹ።
አርባ ምንጭ እና አካባቢዋን በቱሪዝም ዘርፍ በዓለም ተመራጭ ከተማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
በከተማዋ ግንባታው እየተፋጠነ ያለውን የገበታ ለሀገር አርባ ምንጭ ሪዞርት ፕሮጀክት ከባለሀብቶች ጋራ በጋራ ማልማት በሚችልበት ጉዳይ ላይ ውይይት ተካሂዷል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የማዕድን ሚኒስትር እና የገበታ ለሀገር አርባ ምንጭ ፕሮጀክት አስተባባሪ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ፤ የገበታ ለሀገር አርባ ምንጭ ሪዞርት ግንባታ በመገባደድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የአካባቢው ባለሀብቶች በትብብርና በጣምራ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ እንዳለ ገልጸው ይህን እድል እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል።
መንግስት አርባ ምንጭ ከተማንና አካባቢዋን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረው፣ ዘርፉን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የጋሞ ዞንና የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የሥራ ሃላፊዎች፣ አልሚ ባለሃብቶች እንዲሁም የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው የገበታ ለሀገር አርባ ምንጭ ሪዞርት ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ግንባታው እየተፋጠነ ሲሆን በቅርብ ወራትም ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል።