ቀጥታ፡

በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድን በመገንባት ለብልፅግና መረጋገጥ የሚተጋ ማህበረሰብን የመፍጠሩ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል 

ባህር ዳር፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድን በመገንባት ለብልፅግና መረጋገጥ የሚተጋ ማህበረሰብን የመፍጠሩ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለፀ።

22ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን "ትውልድን በስነ-ምግባር ተቋምን በአሰራር" በሚል መሪ መልክት ክልላዊ የማጠቃለያ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሃብታሙ ሞገስ ብልሹ አሰራርንና ሙስናን በዘላቂነት ለመከላከል የትውልድ ስነ-ምግባር ግንባታ ሚናው የጎላ ነው።

በክልሉ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ዘላቂንት ባለው አግባብ መከላከል እንዲቻልም ትውልዱን በስነ ምግባር የማነፅ ስራ በትብብር እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚህም በክልሉ በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድን በመገንባት ለብልፅግና መረጋገጥ የሚተጋ ማህበረሰብን የመፍጠሩ ሂደት ይጠናከራል ብለዋል።

መላ ህብረተሰቡና የዴሞክራሲ ተቋማት በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ እንዲገነባ በማድረግ እያበረከቱት ያለውን ሚና የበለጠ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ባንችአምላክ ገብረማሪያም በበኩላቸው ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት አሰጣጥን ማስፋትና ማጠናከር ግድ ይላል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ማስፋትና እስከ ታች ድረስ ተደራሽ እንዲሆን መረባረብ ይገባል ሲሉም ገልፀዋል።

በክልል ደረጃ፣ በባህር ዳርና ደሴ ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየተተገበረ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ይህም የተገልጋዩን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች በፍጥነት ምላሽ እንዲያገኝ ከማስቻል ባለፈ ከብልሹ አሰራር የፀዳ እንዲሆን ማድረጉን ጠቁመዋል።

በመድረኩም የክልሉ አመራሮች፣ ባለድርሻ አካላትና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም