በሲዳማ ክልል ሰባት የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ከዘርፉ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ሰባት የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ከዘርፉ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው
ሀዋሳ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ሰባት የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማት ከቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የመስህብ ስፍራዎች ቢኖሩም ከቱሪዝም ዘርፍ የሚጠበቀውን ያህል ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆን ሳይቻል ቆይቷል።
ለዚህም እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች በአግባቡ አለመልማትና በመዳረሻ አካባቢዎች ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አለመበራከት በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ አዳዲስ መስህቦችን የመገንባትና ነባሮቹንም በማልማት ለጎብኚዎች ምቹና ተደራሽ ከማድረግ አንጻር በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በዚህም በየዓመቱ የጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ በተጨማሪ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም ከለውጡ በፊት ከነበሩ ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የጎላ ብልጫ እንዳለው መረጃዎች ያሳያሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "በመደመር መንግስት ዕይታ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሀሳብ ለአመራሮች በተሰጠው ስልጠና ላይ ለሀገር ብልጽግና ጉዞ ኢኮኖሚ ያመነጫሉ ተብለው ከተያዙት ውስጥ የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም በዞን ደረጃ አንድ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ ማልማት እንደሚገባ በአጽንኦት መግለጻቸውን ተከትሎ ክልሎች ያላቸውን ዕቅድ በመከለስ ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን አቅደው ወደ ተግባራዊ ገብተዋል።
የሲዳማ ክልልም ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ባሉት አራት ዞኖች ሰባት የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎቸን ለማልማት የሚያስችል ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል።
የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሀላፊና የቱሪዝም ዘርፍ ሀላፊ አቶ አበበ ማሪሞ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ እነዚህን የቱሪስት መዳረሻዎች በአግባቡ አልምቶ ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የቱሪስት ፍላጎትን ለማሟላት በዘርፉ የሚሰጠውን አገልግልት በአይነት፣ በብዛትና በጥራት ከማሳደግ ባለፈ ለቱሪስት መዳረሻዎች ልማት ትኩረት መሰጠቱንም ነው የገለጹት።
በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ በዓለም ባንክና በዓለም ቱሪዝም ድርጅት በተደረገ ጥናት ክልሉ በሰባት የቱሪስት መዳረሻ እና በ11 የቱሪስት እንቅስቃሴዎች ተከፍሎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ሀዋሳ ከተማና አካባቢውን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
የቱሪስት መዳረሻዎቹ ለጎብኚዎች ምቹና የቆይታ ጊዜያቸውን የሚያራዝሙባቸው እንዲሆኑ ለማድረግ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ስራ ትኩረት እንደተሰጠውም አስረድተዋል።
ለአብነት በአሁኑ ወቅት የገራንባ ማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም መዳረሻ ስፍራን የማልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
እንደ አቶ አበበ ገለጻ የሲዳማ ክልል ከአዲስ አባባ ከተማ ያለው ቅርበት፣ የፍጥነት መንገድና የአየር በረራ መኖሩ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ተጨማሪ እድሎች ናቸው።
በእነዚህ ምቹ ሁኔታዎችና የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማልማት በሚከናወኑ ስራዎች የጎብኚዎችን ፍሰት በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማጠናከር እንደሚቻል ተናግረዋል።