አመራሩ በትጋትና በቁርጠኝነት በመስራት ተቋማት ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ሊያደርግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አመራሩ በትጋትና በቁርጠኝነት በመስራት ተቋማት ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ሊያደርግ ይገባል
አሶሳ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ በየደረጃው ያለው አመራር በትጋትና በቁርጠኝነት በመስራት ተቋማት ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባው በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢሳቅ አብዱልቃድር አስገነዘቡ።
በክልሉ 2ኛ ዙር "በመደመር መንግስት ዕይታ የዘርፎች እምርታ" ሰልጣኝ አመራሮች በአሶሳ ከተማ የተለያዩ ተቋማትን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
አመራሮቹ የአሶሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እና የክልሉን ገጠር ቴክኖሎጂ ብዜትና ግብርና መካናይዜሽን ማስፋፊያ ኤጀንሲ የጎበኙ ሲሆን ተቋማቱ በአጭር ጊዜ በሚያመርቷቸው የእንጨት እና ብረታብረት ውጤቶችና ማሽነሪዎች የራሳቸውን የውስጥ ገቢ ማሳደግ ችለዋል።
በተጨማሪም በግብርና ውጤቶች፣ አረንጓዴ ልማት እና በሰው ሀይል ስልጠና ውጤታማ የሥራ እንቅስቃሴ እያከናወኑ እንደሚገኙ የየተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች አብራርተዋል።
ጉብኝቱን አስመልከቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በብልጽግና ፓርቲ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢሳቅ አብዱልቃድር፤ ተቋማቱ በአካባቢያቸው የሚገኙ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በመጠቀም የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ቁሳቁሶችን እያመረቱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ይህም ክልሉን ከወጪ የሚታደግና በራስ አቅም መስራት እንደሚቻል ያመላከተ ነው ብለዋል።
የአመራሩ ትጋትና ቁርጠኝነት ለተያዘው ሀገራዊ ተልዕኮ ስኬታማነት ወሳኝ በመሆኑ በትጋትና በቁርጠኝነት በመስራት ተቋማት ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አመራሮች ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ በሰለጠኑት ልክ የመፈጸም አቅማቸውን ማሳደግና ሰው ተኮር ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ለሁለንተናዊ ብልጽግና መትጋት አለባቸው ብለዋል።
ከጉብኝቱ ተሳታፊ አመራሮች መካከል ጫልቱ ነመራ እና አቶ አጠይብ ማህሙድ፤ በተቋማቱ የተመለከቱት የፈጠራ ስራ በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።
በስልጠናውም ያሉን ፀጋዎች ፍጥነትና ፈጠራ በታከለበት መንገድ በመጠቀም ውጤታማ የልማት ስራዎችን ማከናወን እንደሚቻል ያየንበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
አመራሮቹ በጉብኝታቸው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ አሶሳ ህዳሴ ሙዚየም እና ፍቃዱ ነመራ የተቀናጀ እርሻ ልማት ድርጅትን እንዲሁም ሌሎችን ተመልክተዋል።