ቀጥታ፡

የፓን አፍሪካ ንቅናቄ መሪዎች ልጆች ሕዳሴ ግድብን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ ለፓን አፍሪካ ንቅናቄና ለአፍሪካ ህብረት ምስረታ ጉልህ አበርክቶ ያደረጉ የአፍሪካ መሪዎች ልጆች፣ የልጅ ልጆች ዛሬ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱም የመጀመሪያው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት የፓትሪስ ሉሙምባ ልጅ ሉሙምባ ኦኪቶ ሮላንድ፣ የመጀመሪያው የጋና ፕሬዝዳንት ኩዋሜ ኑኩሩማ የልጅ ልጅ ሜሌጋ ክዋሜ ቶማስ፣ የመጀመሪያው የዛምቢያ ፕሬዝዳንት ኬኔት ካውንዳ ልጅ ካውንዳ ካውቼ፣ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ የልጅ ልጅ ማንዴላ ንዲሌካ እና የታንዛኒያ የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ ልጅ ኔሬሬ ጎድፍሬይ ማዳራካ ይገኙበታል።


 

ጎብኚዎቹ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ የራስን መቻል መገለጫና የተፈጥሮ ሀብቶችን ለእድገት ለመጠቀም ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የለውጥ፣ አይበገሬነትና የሉዓላዊነት ምልክት እንድትሆን ማድረጉን አመልክተዋል።

የፓን አፍሪካ ንቅናቄ መሪዎች ልጆች ትላንት የዓድዋ ድል መታሰቢያ እና የሳይንስ ሙዝየም ቋሚ ኤግዚቢሽንን የጎበኙ ሲሆን ሌሎች የልማት ውጤቶችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም