በጋምቤላ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው
ጋምቤላ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተያዘውን ግብ ለማሳካት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ’’በመደመር መንግሥት እይታ የዘርፎች እመርታ’’ በሚል መሪ ሃሳብ ለከፍተኛ አመራሮች በሰጡት ስልጠና መከናወን ያለባቸውን የልማት ግቦች በዝርዝር ማስቀመጣቸው ይታወቃል።
ከተቀመጡት ግቦች መካከል መሬትን ጦም አለማሳደር እና ተረጂነትን ዜሮ ማድረግ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
በዚህም መሰረት እምቅ የመልማት አቅም ያለው የጋምቤላ ክልል ምርታማነትን በማሳደግ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየሰራ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሪያል ጂንግ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና የመልማት አቅም በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ልማት፣ በቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎች እድገትና ማንሰራራትን እውን የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
በክልሉ በተያዘው የምርት ዘመን ሰብዓዊ ድጋፎችን በራስ አቅም ለመሸፈን ከክልል እስከ ወረዳ በኮታ በመደልደል የግብርና ልማት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
በዘንድሮው ዓመት በግዥና በምርት ዘመኑ ከለማው ከ3ሺህ 403 ሜትሪክ ቶን በላይ መጠባበቂያ የምግብ እህል ክምችት ለመያዝ እየተሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።
ለመጠባበቂያ ለሚያዘው የምርት ማከማቻ አምስት መጋዘኖችን የማዘጋጀትና የማደስ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
የጋምቤላ ወረዳ አስተዳዳሪ ኡቶንጊ ኡላሚ፤ ሰብዓዊ ድጋፎችን በራስ አቅም ለመሸፈን የተያዘውን ግብ ለማሳካት አመራሩ ህዝቡን በማስተባበር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመኸር እርሻ የተከናወነው የተጠናከረ ስራ የውሃ ሸሽ፣ የመስኖና ሌሎች የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በበጋው ወራትም ተጠናክሮ መቀጠሉን አረጋግጠዋል።