ቀጥታ፡

የባህር በር ጉዳይ የትውልዱ ጥያቄ በመሆኑ ወደ ተግባር እስኪቀየር አጀንዳው መቀጠል አለበት

ጂንካ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ የባህር በር ጉዳይ የትውልዱ ጥያቄ በመሆኑ ወደ ተግባር እስኪቀየር አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት ሲሉ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ መምህራን አመለከቱ።

የቀይ ባህር ጉዳይ ከታሪካችን፣ ከስልጣኔያችን፣ ከሀገረ-መንግስት ስሪታችን፣ ከደህንነታችን እንዲሁም ከምጣኔ ሃብታዊ ራዕያችን ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው።

ለዚህም ነው የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከህግ፣ ከሞራልም ሆነ ከዲፕሎማሲ አንፃር ትክክለኛ ምላሽን ይሻል በዚህም አጀንዳውን የምዕራቡም ሆነ የምስራቁ ዓለም ፍትሃዊነቱን አጢኖ ድጋፉን የሰጠው ጉዳይ ነው።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄው በሁሉም መስፈርት ተገቢና የትውልዱ ጥያቄ በመሆኑ ወደ ተግባር እስኪቀየር ድረስ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።  

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ጌታቸው ብርሃኑ፥ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በየትኛውም መስፈርት ተገቢነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ህጋዊ፣ ታሪካዊና መልክዓ ምድራዊ መብት የነበራት ቢሆንም ምክንያቱ እና ውሳኔ ሰጪው ባልታወቀበት ሁኔታ ከባለቤትነት እንድትርቅ ተደርጋ ለዓመታት መዝለቋ የሚቆጭ ነው ብለዋል። 

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ባልሆነና አግባብነት በሌለው መልኩ ያጣችውን የባህር በሯን ለማስመለስ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረጓም ትክክለኛ አካሄድ ነው ብለዋል። 

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ምስክር ከተማ በበኩላቸው የባህር በር ጉዳይ የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ አጀንዳ መሆን የለበትም ብለዋል። 

በታሪክ ተወቃሽ ላለመሆንም የባህር በር ጉዳይን የሁልጊዜ አጀንዳ በማድረግ መሟገትና ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር እንደሚገባ ተናግረዋል። 

የባህር በር ጥያቄ ፖለቲካዊ ትርጉም ሊሰጠው እንደማይገባ ጠቅሰው ጥያቄው የትውልዱ የዘመናት ጥያቄና የህልውና ጉዳይ መሆኑ ተሰምሮበት የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለፁት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፖለቲል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ጌታቸው ብርሃኑ ናቸው። 

በተለይ ምሁራን እና የማህበረሰብ አንቂዎች አጀንዳው የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመው፥ የኢትዮጵያን ዕውነታ ለአለም ማህበረሰብ በማሳወቅ ለስኬቱ የበኩላቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም