የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል
ሮቤ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ)፦ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በአካባቢው እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድና የቱሪዝም መሰረተ ልማት ስራዎች ለቱሪስት ፍሰቱ መጨመር ምክንያት መሆናቸውም ተመልክቷል።
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከ2ሺህ ስኩዬር ኪሎ ሜትር በላይ ስፍራን ያካለለና የበርካታ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፍ ባለቤት ነው።
በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ፓርኩ የደጋ አጋዘን፣ ቀይ ቀበሮ፣ ድኩላ፣ የባሌ ጦጣና ሌሎች የዱር እንስሳትና አዕዋፋት መገኛ ነው።
የፓርኩ ኃላፊ ሻሚል ከድር እንደተናገሩት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 3ሺህ 690 የሀገር ውስጥና የውጪ ቱሪስቶች ፓርኩን ጎብኝተዋል፡፡
ከጎብኚዎቹ መካከል 45 በመቶ የሚሆኑት የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች መሆናቸውን አመልክተው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ17 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
የቱሪስቶች ቁጥር መጨመሩ የፓርኩንና የአካባቢውን ህብረተሰብ ገቢ እንዲጨምር ማድረጉን ገልፀው ለአብነትም በሩብ ዓመቱ በኢኮ ቱሪዝም የተደራጁ ማህበራት ያገኙት ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ገቢ ካለፈው ዓመት በ2 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱን አስረድተዋል፡፡
የፓርኩ ገቢ በሩብ ዓመቱ 600ሺህ ብር መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ካለፈው ዓመት በ200 ሺህ ብር ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ በቋሚ ቅርስነት መመዝገቡና ፓርኩ ይበልጥ እንዲተዋወቅ መደረጉ ለቱሪስቶች ቁጥር መጨመር ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በአካባቢው እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድና የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች ሌላው ለፍሰቱ መጨመር በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው ብለዋል።
የባሌ ተራሮችን ጨምሮ በዞኑ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን በማልማትና ይበልጥ በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዞኑ ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የቱሪዝም ልማትና ማስፋፊያ ቡድን መሪ ሽብሩ አብዶ ናቸው።
በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለመዳረሻዎች ልማት የሰጡት ትኩረት ዘርፉን እያነቃቃ መሆኑን አመልክተዋል።
በፓርኩ ክልል ለቱሪስቶች የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጠው የኢኮ ቱሪዝም ማህበር ስራ አስኪያጅ መሐመድ ከድር የቱሪስቶች ፍሰት መጨመር ለሥራችን አጋዥ ነው ብለዋል።
የማህበሩ አባላት ለቱሪስቶች በቅሎ በማከራየትና ጓዝ በመጫን በቀን በሚያገኙት ገቢ ህይወታቸውን እየመሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በፓርኩ ክልል በቱሪስቶች እጀባ ስራ የተሰማሩት ሌላው የአካባቢው ነዋሪ ሁሴን ከማል ህብረተሰቡ ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን መንግስት ያመቻቸው ስምሪት ፓርኩን በባለቤትነት እንድንጠብቅና እንድንንከባከብ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል ብለዋል፡፡