የአገልግሎት ጥራትና የተደራሽነትን መጠን የሚያሳድጉ ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአገልግሎት ጥራትና የተደራሽነትን መጠን የሚያሳድጉ ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ):- በኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአገልግሎት ጥራትን የሚያሻሽሉና የተደራሽነትን መጠን የሚያሰፉ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በሌላ በኩል ባለፉት አራት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበው የኤሌክትሪክ ሀይል ከ46 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት ተቋሙ የሚሰጠውን አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ለማሻሻል በርካታ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።
በዚህም የጣቢያዎችን ኃይል የመሸከም አቅም ለማሳደግ እና የጣቢያዎችን መቆጣጠሪያ ሲዊቾች በመቀየር ተጨማሪ ደንበኞችን እንዲያስተናግዱ የማድረግ ስራዎችን መከናወናቸው አንስተዋል።
እንዲሁም አዳዲስና ተጨማሪ አቅም ያላቸው ትራንስፎርመሮች የመቀየር ስራዎች መሰራታቸውንም ጠቅሰዋል።
በዚህም የአገልግሎት ጥራት የማሻሻልና ተደራሽነትን በማስፋት ተጠቃሚዎች ያለ ምንም ችግር አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
አዋሽ ሰባት፣ ወልቂጤ፣ ኮምቦልቻ፣ ወላይታ ሶዶ፣ አለም ገና ከተማና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች በዘመናዊ መቆጣጠርያ ሲዊች መቀየራቸው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመርተውን የኤሌክትሪክ ሃይል በዋነኝነት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያቀርብ መሆኑ አቶ ሞገስ ጨምረው ገልፀዋል።
በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ላሉ ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች፣ ለኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር እና በማይኒንግ ዘርፍ ተሰማርተው ክፍያን በዶላር ለሚፈፅሙ አካላት እንደሚያቀርብ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል ለውጭ ኤሌክትሪክ ሃይል ፈላጊ ሀገራት የሚያቀርብ ሲሆን በዋነኝነት ኬንያ፣ ጂቡቲ እና ታንዛንያ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
በዚህም በ2018 በጀት አመት ባለፉት አራት ወራት ለኬንያ፣ ጁቡቲ እና ታንዛንያ በሽያጭ ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል 46 ነጥብ 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልፀው ይህም ከእቅዱ አንፃር 25 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል።