ቀጥታ፡

የመደመር መንግስት እይታ ሀገርን በመለወጥ ህዝብን ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ለተግባራዊነቱ እንተጋለን

ሮቤ፤ ህዳር 27/2018 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግስት እይታ ሀገርን በመለወጥ ህዝብን በቀጥታ ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት እንተጋለን ሲሉ የባሌ ዞን አመራሮች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ!” በሚል መሪ ሃሳብ ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ሰፊ እና ጥልቅ የሆነ ስልጠና መስጠታቸው ይታወቃል። 

በስልጠናው በተለይም በመንግስት አስፈፃሚ አካላት የሚተኮርባቸውን ግቦች በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን በመፍጠርና በመፍጠን የሚተገበር ቁርጠኛ አመራር መኖር እንዳለበትም አጽዕኖት ሰጥተዋል። 

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የባሌ ዞን አመራሮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ አቅጣጫዎች ከአመራሩ ባሻገር ሀገርን መለወጥ የሚችሉና ህዝብን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስለመሆናቸው አንስተዋል። 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልይ መሐመድ እንዳሉት የተሰጠው ሥልጠና በአካባቢያችን የሚገኙ እምቅ ሃብቶችን በመፈተሽ ለህዝብ ጥቅም ለማዋል የሚያግዝ ነው። 

በተለይ በዞኑ አርሶ አደሩ ከዘልማዳዊ አሰራር ተላቆ ወደ ሜካናይዜሽን እንዲሸጋገር በኩታ ገጠም እርሻና በሌሎችም ኢንሼቲቮች የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ለማስቀጠል ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል። 

በዞኑ በአሁኑ ወቅት በመኸሩ የምርት ወቅት የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ እየለማ የሚገኘው ከ528 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይህንኑ የሚያሳይ ነው ብለዋል። 

በዘርፎች እመርታ ዙሪያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና እና የስራ አቅጣጫ ለለውጥና ማንሰራራት ወሳኝ መሆኑን የተረዳንበት ነው ያሉት ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ኃይሌ ናቸው። 

በተለይ በዞኑ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና ሰፊ የሰው ኃይል በማስተባበር የታለሙትን የልማት ግቦች ለማሳካት የተሰጣቸው ሥልጠና ትልቅ ስንቅ እንደሚሆናቸውም አመልክተዋል። 

በባሌ ዞን የመስክ ምልከታ ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ኦቱካና ኦዳ (ዶ/ር) ይህንኑ ሀሳብ ያጠናክራሉ። 

በዞኑ ባደረጉት የመስክ ምልከታ መንግሥት የአርሶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ ተግባራዊ እያደረጋቸው የሚገኙ የግብርና ኢኒሼቲቮች የሚታይ ለውጥ ማስመዝገብ መጀመራቸውን መመልከታቸውን አስታውሰዋል። 

እንዲሁም በተግባር እያታዩ የሚገኙ ስኬቶች የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያ ብልጽግና ማረጋገጫ መንገድ መሆኑን የሚያሳዩ እንደሆነ ተናግረዋል። 

በተለይ የአካባቢው አመራሮች ከግብርና ምርምር ማዕከላት እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት የአርሶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ እያደረጉት የሚገኙት ጥረት በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም