ቀጥታ፡

በፕሪሚየር ሊጉ አስቶንቪላ ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2018(ኢዜአ):- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት አስቶንቪላ እና አርሰናል ዛሬ የሚያከናውኑት ጨዋታ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ትኩረት ስቧል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 በቪላ ፓርክ ስታዲየም ይካሄዳል።

አስቶንቪላ በ27 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ሲይዝ አርሰናል በ33 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።

በስፔናዊው አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬ የሚመራው አስቶንቪላ በሊጉ ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች ስምንቱን ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።

በጨዋታዎቹ 20 ግቦችን ሲያስቆጥር 14 ጎሎችን አስተናግዶ በ27 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው አርሰናል በበኩሉ በውድድሩ ካከናወናቸው 14 ጨዋታዎች መካከል 10ሩን ሲያሸንፍ ሽንፈት ያስተናገደው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።

27 ግቦችን በ14ቱ ጨዋታዎች ከመረብ ሲያሳርፍ ሰባት ጎሎች ተቆጥረውበታል።

በስፔናዊው ማይክል አርቴታ የሚሰለጥኑት መድፈኞቹ ሊጉን በ33 ነጥብ እየመሩ ነው።

ሁለቱ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ61ኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 60 ጨዋታዎች አርሰናል 39 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ አስቶንቪላ 13 ጊዜ ሲያሸንፍ ስምንት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

አርሰናል በጨዋታዎቹ ላይ 125 ግቦችን ሲያስቆጥር አስቶንቪላ 73 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ባለፉት 10 የሊግ ግንኙነታቸው አርሰናል አምስቱን ሲያሸንፍ አስቶንቪላ ሶስት ጊዜ ድል ቀንቶታል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

በውድድር ዓመቱ ደካማ ጅማሮ ካሳየ በኋላ በጠንካራ አቋም ላይ የሚገኘው አስቶንቪላ በዛሬው ጨዋታ የሊጉን መሪ ይፈትናል ተብሎ ይበቃል።

በጠንካራ ብቃት ላይ የሚገኘው አርሰናል በጨዋታው ላይ የሊጉን መሪነት ለማጠናከር የመጨረሻ ምርጥ ብቃቱ ላይ መገኘት ይኖርበታል።

የ43 ዓመቱ ፒተር ባንክስ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።


 

በሌሎች መርሃ ግብሮች በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንችስተር ሲቲ ከሰንደርላንድ ጋር ቅዳሜ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በኢትሃድ ስታዲየም የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል።

ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ ሊድስ ዩናይትድ ከወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል ጋር ይጫወታል።

ኤቨርተን ከኖቲንግሃም ፎረስት፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ከበርንሌይ፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከብሬንትፎርድ እና ቦርንማውዝ ከቼልሲ በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም